ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ታግዞ በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ታግዞ በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እየሰራ ነው
ደሴ፤ ህዳር 10/2017 (ኢዜአ)፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ታግዞ በማጎልበት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ዩኒቨርስቲው አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የሲቪክ ማበልጸጊያ ማዕከል ዛሬ በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በምርምር በማጎልበት እያገዘ ነው፡፡
በዚህም የወሎን የመቻቻል፣የአንድነት፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌትነትን በማጠናከርና በማስቀጠል ለትውልድ በማስተላለፍ ሰላም እንዲሰፍን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ስለ ሰላም አስፈላጊነት ግንዛቤ በመፍጠር፣ በማስተማር፣ ስልጠና በመስጠትና በሌሎችም ተግባራት ዙሪያ አበክሮ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ በአበጋር፣ በሽምግልና፣ በባህላዊ እርቅ ስርዓትና በሌሎችም ሀገር በቀል እውቀቶች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሐይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ሌሎችንም በማሳተፍ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ለዚህም ያግዝ ዘንድ አጋር አካላትን በማስተባበር የሲቪክ ማበልጸጊያ ማዕከል ተመቻችቶ ዛሬ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ማንኛውም ሀሳብ ያለው ሁሉ በማዕከሉ በመምከር መፍትሄ ማፈላለግ እንዲችል እድልን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ማዕከሉ በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ ለኮንፈረንስ፣ ለውይይትና ለሌሎችም ገጽ ለገጽ ንግግሮች የተመቻቸና ግብዓት የተሟላለት እንደሆነም አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሰላምና ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና የልጅ እያሱ የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የሐይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ ምሁራንን በማሳተፍና በማወያየት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገ ሲሆን ውጤትም እየጠመዘገበ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪክ ተሳትፎ ፕሮግራም ዳይሬክተር ወይዘሮ ብሌን አስራት እንዳሉት፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡
በፕሮግራሙ በተለያዩ አካባቢዎች የሲቪክ ማበልጸጊያ ማዕከልን በማመቻቸት ህብረተሰቡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተመካክሮ፣ ተወያይቶና መፍትሄ አፍልቆ ሰላሙን እንዲጠብቅ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የደሴ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የከተማው የሐይማኖት ፎረም ሰብሳቢ ሊቀ ጠበብት ሲራክ መለሰ በበኩላቸው፤ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በችግሮች ዙሪያ በጋራ የመፍትሄ ሀሳብ በማመንጨት ለከተማችን ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መምከር እንድንችል የማዕከሉ ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ እንድሪስ በሽር ናቸው፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ምሁራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።