የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በምቹና ቀልጣፋ አሰራር አትራፊ ገበያ ሆኗል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/ 2017(ኢዜአ):-በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችና ቀልጣፋ አሰራሮች የወጪ ንግድ ዘርፉን አትራፊ ገበያ አድርጎታል ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን በአይነት፣ በብዛትና በጥራት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለችም ብለዋል። 

ከ24 አገራት የተውጣጡ ከ120 በላይ የውጭ ኢንቨስተሮች የተሳተፉበት 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ሁሉን አብቃይ፣ አይነተ ብዙ የአየር ንብረት ባለቤት እንዲሁም ለተለያዩ የግብርና ምርቶች የተመቸ ስነ ምህዳር ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

በተለይም የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎችን የማምረት አቅም እንዳላት አንስተው ለአምራቾች የተለያዩ ማበረታቻዎች እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ ለዘርፉ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን አንስተው በዚህም በዓመት እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እየተገኘበት ነው ብለዋል፡፡

በተለይም በባቄላ፣ ምስር እና ቦለቄ ምርቶች ብዛት ከዓለም ቀዳሚ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተው፤ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በአይነት፣ በብዛትና በጥራት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ጀምረናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቀይና ነጭ ሰሊጥ በማምረት እንዲሁም ከአኩሪ አተር የሚገኘውን ተረፈ ምርት ወደ ውጭ እየላከች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ካላት እምቅ አቅም አንጻር በቂ ባይሆንም ባለፉት ዓመታት የታዩት ለውጦች ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችና ቀልጣፋ አሰራሮች የወጪ ንግድ ዘርፉን አትራፊ ገበያ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እየሰራች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይሄውም ለዘርፉ ተዋንያን አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያም በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራር ፈጥሯል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አካዳሚ በመገንባት የንግድ መሰረታውያንን በማሰልጠን የዘርፉን የተዋንያን አቅም እየገነባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የወጭ ንግድ ዶላር ከማግኘትም ባሻገር እስከ 30 በመቶ ትርፍ የሚገኝበት አትራፊ ንግድ ሆኗል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤዳኦ አብዲ፤በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የኢኮኖሚው ዋልታ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ 80 በመቶ የሚሆነውን የሰው ሃይል መያዙን ጠቅሰው፤ 75 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝትም ከግብርና ምርቶች ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በ10 በመቶ እድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም