ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ትኩረት በተሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/ 2017(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ትኩረት በሰጣቸው የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች እንዲሠማሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጥሪ አቀረቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከስዊዘርላንድ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ስታልደር ጋር በወቅታዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ስዊዘርላንድ አምስተኛዋ የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች መዳረሻ መሆኗንም አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን በመግለጽ የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ትኩረት በሰጣቸው የማዕድን፣ የማምረቻ፣ የግብርና ምርቶች ማቀናበሪያ እና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ እንዲሠማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላትን የቴክኒክ ትብብርም የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሠራ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።


 

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው ኢኮኖሚዋ እና የሕዝብ ቁጥሯን ታሳቢ በማድረግ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገችው ያለውን ጥረትም ለረዳት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ በአረንጓዴ አሻራ እያከናወነች ያለውን ተግባር፣ በሽግግር ፍትህ እና በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዙሪያ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ላይም ገለጻ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ፀጥታ የምታደርገውን አስተዋፅእ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደር ምስጋኑ አረጋግጠዋል።

የስዊዘርላንድ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ስታልደር በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ረዳት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እየተወጣቸው ያለውን ሚና በተለይም አሸባሪው አል ሽባብን በመዋጋት ረገድ እያደረገችው ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ እና ረዳት ሚኒስትሩ ፊሊፕ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም