ሀገራዊ ሪፎርሙ አጠቃላይ ለባንኮችና የፋይናንስ ሴክተር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ሪፎርሙ አጠቃላይ ለባንኮችና የፋይናንስ ሴክተር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ሪፎርሙ አጠቃላይ ለባንኮችና የፋይናንስ ሴክተር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ውጤቶች እና ለዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሸዴ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን ጨምሮ ሌሎች የመንግስትና የግል የፋይናንስ ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፤ ሀገራዊ ሪፎርሙ አጠቃላይ ለባንኮችና የፋይናንስ ሴክተር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
ለዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርን የተከተሉ አዳዲስ አሰራሮችን የመተግበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
በመሆኑም በቀጣይ አጠቃላይ ባንኮችና የፋይናንስ ዘርፍ በውጤታማነት ለመዝለቅ በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከለውጡ በኋላ ተግባራዊ የሆነው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ አዳዲስና ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ ምንጭ እውን በማድረግ ለብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች ትኩረት የተሰጠበት መሆኑ ይታወቃል።