ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት የትውልዱ ደማቅ አሻራ ያረፈበትና የመንግስት የመፈፀም ቁርጠኝነት የታየበት ነው-የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት የትውልዱ ደማቅ አሻራ ያረፈበትና የመንግስት የመፈፀም ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮችና የሁሉም ክልልና ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል።


 

የፓርቲው አመራሮች የግድቡን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታና የተለያዩ ክፍሎቹን የጎበኙ ሲሆን ሁሉንም የሚያኮራ የትውልዱ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት የትውልዱ ደማቅ አሻራ ያረፈበትና የመንግስት የመፈፀም ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ፤ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በትውልድ ቅብብሎሽ ህልማቸውን የፈቱበት ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከገንዘብ፣ጉልበትና እውቀታቸው ባሻገር የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት የጋራ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት በመሆኑንም አንስተዋል።

ለግድቡ ግንባታ መሳካት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት ልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለስኬት ያበቃው መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሃብትና ቋሚ ቅርስ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በጋራ ከሰሩና በአንድነት ከቆሙ የማይቻል ነገር፤ የማይሳካ ልማትና የማይፈፀም ውጥን እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤የህዳሴ ግድብ "የህልም ጉልበት ለእምርታው እድገት" የሚለው ፅንሰ ሃሳብ በተግባር የተገለጸበት የህዝብ ሃብት መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ እቅድና ህልም የተፈጥሮ ሀብቷን በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚሁ መንገድ የምትቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ የዜጎች ሁሉ አሻራ ያረፈበት የአብሮነት ማሳያና ከጋራ ትርክቶቻችን መካከል በማሳያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፤ የግድቡ መገንባት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያረጋግጥ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፥ ግድቡ የሀገር ሃብትና የሀገር ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም