የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ እሴት በመጨመር የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ እሴት በመጨመር የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ):- የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ዘርፉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለተለያዩ የግብርና ምርቶች የተመቸ አየር ንብረትና ሥነ-ምህዳር አላት።
ኢትዮጵያ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳላት ገልጸው፣ መንግሥት ይህንን አቅም ለመጠቀም ለዘርፉ ተዋናዮች ማበረታቻ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ የአገር በቀል ኢኮኖሚና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ለማበረታታት ትልቅ አቅም መፍጠሩንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለዘርፉ ተዋንያን አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ገቢራዊ ያደረገችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የውጭ ባለኃብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የአገሪቱን ዓለም አቀፋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ያጎለብታል ብለዋል።