አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ከሩሲያው ስፑትኒክ ዜና አገልግሎት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ከሩሲያው ስፑትኒክ ዜና አገልግሎት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ከሩሲያው ስፑትኒክ የአፍሪካ ዲቪዥን ኃላፊ ቪክቶሪያ ቡዳኖቫ እና ከስፑትኒክ የውጭ ቋንቋዎች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዋና አዘጋጅ ኦልጋ ሊጎሶር ጋር ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የስፑትኒክ ኃላፊዎች ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ስፑትኒክ በኢትዮጵያ ቢሮ በመክፈት በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የዲጂታል ዜና ለተገልጋዮች ለማድረስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸው ለዚህም በሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
በአምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር) በኩልም የሚዲያ ተቋሙ በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤቱን ከፍቶ እንዲንቀሳቀስ ድጋፍ እንደሚደረግ መገለጹን በሞስኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል ቀደም ሲል መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም ያደረጉት የስምምነት ፊርማ ሁለቱም የዜና አገልግሎቶች ተጠቃሽ የሆኑ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችንና በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚካሄዱ ትልልቅ ኩነቶችን የዘገባ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያስችል ነው።
የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚመለከቱ መረጃዎችን እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ ዜናዎችን በእንግሊዘኛና በአረብኛ ቋንቋዎች ይለዋወጣሉ።