ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዋን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ በሞሮኮ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 8 ስድስተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታዋን ዛሬ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ታከናውናለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኘው ስታድ ማርትያር ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቀናት በፊት በምድቡ ባደረገው አምስተኛ ጨዋታ በታንዛንያ 2 ለ 0 መሸነፉ ይታወቃል።

ብሔራዊ ቡድኑ በምድቡ እስከ አሁን ባደረገቻቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር 11 ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በአንድ ነጥብ በምድቡ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ዋልያዎቹ በታንዛንያ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኋላ ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ መሆናቸው አይዘነጋም።

በ48 ዓመቱ ፈረንሳዊ ሰባስቲያን ዲሳብሬ የሚመራው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በ12 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ይታወቃል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከቀናት በፊት በምድቡ ባደረገው አምስተኛ ጨዋታ በጊኒ 1 ለ 0 ተረቶ በማጣሪያው የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

ኢትዮጵያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምድቡ በነበራቸው የመጀመሪያ ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።


 

በዚሁ ምድብ ታንዛንያ እና ጊኒ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ጊኒ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ፣ ታንዛንያ በሰባት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ጨዋታው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ተከትሎ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈውን ቀሪ ቡድን ይወስናል።

ጊኒ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያሳልፋት ሲሆን ታንዛንያ ማሸነፍ ብቻ የሞሮኮ ትኬቷን እንድቆርጥ ያደርጋታል።

አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ አንጎላ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ማሊ፣ ቤኒን ኮሞሮስ፣ዛምቢያ፣ ዚምባቡዌ  እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስከ አሁን በአፍሪካ ዋንጫው መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።

ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያልፉ ቀሪ ሶስት አገራት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።

48 አገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን የማጣሪያ ውድድሩ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም