ብልፅግና የህዝቦችን አንድነትና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ እየተጋ ያለ ትልቅ አቅም ያለው ፓርቲ ነው - የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ ብልፅግና የህዝቦችን አንድነትና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ እየተጋ ያለ ትልቅ አቅም ያለው ፓርቲ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የፓርላማ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት "የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ የፓርቲውን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አክብረዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እና የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አገኘሁ ተሻገር፤ ብልፅግና ፓርቲ የህዝቦች የለውጥ ፍላጎት የወለደው ህብረ ብሔራዊና አካታች ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን የፖለቲካ አውድ በመቀየር በሁሉም አቅጣጫ የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ በተግባር ያረጋገጠ አካታች ፓርቲ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በሂደት አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት የህዝቦችን አንድነትና የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት እውን ለማድረግ በትጋት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከምስረታው ጀምሮ እስከአሁን የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት በተጨማሪ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ በላቀ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተስፋዬ ቤልጅጌ (ዶ/ር)፤ ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ የህዝብን ተጠቃሚነትና የሀገርን ብልፅግና ለማረጋገጥ ህዝብን በማስተባበር በትጋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሂደትም በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገብ የቻለ ፓርቲ መሆኑን አንስተው በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ አዲስ ታሪክ እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግና ወደተሟላ የትግበራ ምዕራፍ በማሸጋገር የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲፈጠር ማደረጉንም ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሰነቀውን ራዕይ እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ እና የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ኡመድ፤ ፓርቲው የሴቶችን እውነተኛ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና ከላይኛው እስከ ታችኛው የመንግስት እርከን የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ በተግባር ማረጋገጥ የቻለ ፓርቲ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ እና የብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሎሚ በዶ፤ ብልፅግና የገጠሙትን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ያለ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

የሴቶችን የፖለቲካ፣ ማህበራዊና የልማት ተሳትፎ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ተግባራት ማከናወኑንም ገልጸዋል።

የፓርላማ ልዩ ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ኃላፊ መሠረት ኃይሌ፤ ሕብረ-ብሔራዊና አካታችነትን መሰረት ያደረገው ብልፅግና ፓርቲ ፈተናዎችን በመጋፈጥ በብዙ ስኬቶች ታጅቦ ቀጥሏል ብለዋል።

በቀጣይም "ባለህልም መሪዎች፣ ትጉህ አባላት ለህዝባችን ስኬት፣ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲያችን ለሕብረ ብሔራዊ ሀገራችን!" የሰነቅነውን ህልም እውን ለማድረግ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም