ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ይገባል
አዲስ አበባ፤ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር እና ባህላዊ ሀብቶችን በማልማት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር ገለፁ።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባ ምንጭ ከተማ ይከናወናል።
ምክር ቤቱ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት የሚቆይ ልዩ ልዩ ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡበት ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በይፋ አስጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልቃድር በዚህ ወቅት የህዝቦችን ብዝሀነት እና አብሮነት ባረጋገጠ መልኩ የኢትዮጵያ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲከበር መቆየቱን አውስተዋል።
በዓሉ ዘላቂነት ያለው ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሁሉም ዜጋ የማይተካ ሚና ማበርከት እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አብሮ የመኖር እሴት ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከርና ያሉንን ባህላዊ ሀብቶች በማልማት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻገር የቤት ስራችን ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የተዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር እንደ ሀገር ያሉን የባህል ሀብቶች የሚታዩበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ያጠናክራል ብለዋል።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ 150 ተሳታፊዎች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡
የተለያዩ የባህል አልባሳት፣ልዪ ልዪ የእደ ጥበብ እና የቆዳ ውጤቶች እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለሸማቹ ማህበረሰብ ለገበያ ከቀረቡት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
በመርሀ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።