ቀጥታ፡

ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ የአምራቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት የማጎልበት ቅንጅታዊ ሥራ እየተሰራ ነው

ድሬደዋ፤ ህዳር 9/2016 (ኢዜአ)፦ ከቡና ምርት የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ የአምራቹን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማጎልበት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከቡና የሚገኘውን ገቢ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል። 


 

የምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበትና የቡና ምርታማነትና ጥራትን ለማሳደግ የሚያግዝ ውይይት ዛሬ በድሬደዋ ተካሄዷል። 

ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አገራዊ የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት የቡና ምርታማነትና ጥራትን በማሳደግ በአለም አቀፍ ደረጃ  ተወዳዳሪ ለመሆን በትኩረት እየተሠራ ይገኛል። 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከቡና ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ በተከናወኑ የተቀናጁ ጥረቶች በዓመት ይገኝ የነበረውን ስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። 

የተጀመረውን የቡና ሪፎርም ስራ በተቀናጀ እና በላቀ ውጤት ለማሳደግና የቡና አምራቹን ማህበረሰብ ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አዲስ ፖሊሲ በመተግበር ላይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። 

በዘርፉ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን በማሳካት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከቡና ምርት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ወደ አራት ቢሊዮን ደላር ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። 

የቡናን ምርታማነት ማሳደግና ጥራቱን ጠብቆ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሁላችንም ታላቅ አገራዊ የሪፎርም ኃላፊነት መሆኑን በመረዳት ለስኬታማነቱ  መረባረብ አለብን ያሉት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ናቸዉ። 


 

ከምስራቅ ተጎራባች ክልሎች የሚመረተው ቡና ጥራቱን ለመጠበቅና ከኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ነፃ እንዲሆን ውይይቱ ወሳኝ አበርክቶ አለው ብለዋል። 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ አሚን በበኩላቸው ክልሉ ቡናን ምርታማነቱን በማሳደግ እንዲሁም ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ እንዲቀርብ የሚያደርጉ አበረታች ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይ ቡናን ከኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች በማፅዳት ለገበያ ቀርቦ የአምራቹ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም