ቀጥታ፡

የተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ የህዝብና የሀገርን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሊታይ ይገባል

አዲስ አበባ፤ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦የተሻሻለው የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ የህዝብና የሀገርን ጥቅም በዘላቂነት በሚያስጠብቅ መልኩ ሊታይ እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

ቋሚ ኮሚቴው የመገናኛ ብዙሃን ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የአስረጂዎች የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሃመድ እድሪስ፥ አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያትና የረቂቁን ይዘት መሰረታዊ ሃሳቦች በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

ለውጡን ተከትሎ የተሻሻለውና አሁን በስራ ላይ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አዋጁ የሚዲያና የሃሳብ ነጻነትን ያከበረ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ከአዋጁ በፊት በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ቁጥር በፊት 150 እንደነበር አስታውሰው፥አሁን ላይ ከ280 በላይ ደርሷል ብለዋል።

ቀደም ሲል ያልነበሩ 51 የሃይማኖት ቴሌቪዥኖች ፈቃድ እንዲያገኙና ፈቃድ የወሰዱና ያልወሰዱ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን በኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲሰሩ እድሉን ማስፋቱንም ነው ያብራሩት።

በተጨማሪም ሙሉ ለሙሉ በሚዲያ አካላት የሚተዳደር ገለልተኛ የሚዲያ ካውንስል ተቋቁሞ በስራ ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አዋጁ ከመውጣቱ በፊት 6 የነበሩ የሲቪል ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት ቁጥራቸው ጨምሮ 44 መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በ39 ቋንቋዎች የነበረው የሚዲያ ስርጭትም በአሁኑ ወቅት 60 በመድረስ የብዝሃ ቋንቋ ተደራሽነት መስፋቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሚዲያ ኢንዱስትሪው አዋጁ ውጤት ያመጣ ቢሆንም ተጠያቂነትን በማስፈን የህዝብና የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ለባለስልጣኑ አዋጁ የሰጠው ስልጣን ክፍተት በመኖሩ ማሻሻያ ማስፈለጉን አስረድተዋል።

በመድረኩም ከቋሚ ኮሚቴው አባላትና ከምክር ቤቱ የህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት በረቂቅ አዋጁ ላይ የተለያዩ ጥያቄና አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

የባለስልጣኑ የህግ አገልግሎት ዴስክ ሃላፊ ቆንጅት ታምራት፤የሌሎችን መብትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ አሰራር ለመዘርጋት በረቂቁ መቀመጡን ገልጸዋል።


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ በበኩላቸው የመገናኛ ብዙሃንን አቅም በመገንባት የተጠያቂነት አሰራርን መዘርጋት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

በምክር ቤቱ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

ለብሔራዊ መግባባትና የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሚዲያው ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ እየተደረገ ያለውን ሪፎርም እና ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመጨመር በቀጣይ በጥናት ተለይቶ እንዲቀርብም አሳስበዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም