ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አመሰገኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አመሰገኑ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ቅድሚያ በመስጠት በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ምስጋና አቅርበዋል።
የቀድሞው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት አህመድ መሀመድ መሀሙድ የቀብር ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በሀርጌሳ ተፈጽሟል፡፡
በቀብሩ ላይም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የተመራ የመንግስት የልኡካን ቡድን ተገኝቷል።
የልኡካን ቡድኑ በዚህ ወቅት በኢፌዲሪ መንግሰትና ሕዝብ ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው የሶማሊላንድ ሕዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂም የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ኢትዮጵያ ለጎረቤት ቅድሚያ በመስጠት በአስቸጋሪ ወቅቶች ጭምር ከሶማሊላንድ ሕዝብ ጎን በመሆን ላሳየችው ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አህመድ መሀመድ መሀመድ ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ኖረዋል።
በሕዝቦች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲዳብር እና ወንድማማችነት እንዲፀና ላበረከቱት በጎ አስተዋጽኦም አቶ አደም ፋራህ በኢፌዲሪ መንግስት ስም ያላቸውን ክብር እና ምስጋና ገልፀዋል።