ቀጥታ፡

የገንዘብ ሚኒስትር እና ወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2017 (ኢዜአ):- የገንዘብ ሚኒስትር እና ወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት የፋይናንስ ሀብት ማፈላለጊያ አማራጮችን ማስፋት ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና የወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት የአፍሪካ ከተሞች ዳይሬክተር አክሊሉ ፍቅረስላሴ (ዶ/ር) ናቸው።

አቅም ግንባታ፣ ፖሊሲ ጥናት፣ አጋርነት፣ ሀብት ማሰባሰብ፣ የትብብር ማዕቀፎችን ማጠናከር እና ፈጠራ የታከለባቸው የፋይናንስ ሀብት ማፈላለጊያ አማራጮችን መቅረጽ ሁለቱ ተቋማት በስምምነቱ አማካኝነት ከሚሰሩባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ለመስራት ያላውን ፍላጎት አድንቀዋል።

ስምምነቱ የሚኒስቴሩን አቅም የማጎልበት፣ ዘላቂ የፋይናንስ ልማት ማረጋገጥ ስራዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ማፈላለግና ሌሎች ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

የወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት የአፍሪካ ከተሞች ዳይሬክተር አክሊሉ ፍቅረስላሴ (ዶ/ር) ኢኒስቲትዩቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ግቦች እንዲሳኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የፊስካል ፖሊሲ፣ የፋይናንስ እቅድ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስና ድርድር ፣ የበጀት ዝግጅትና ለሌሎች አገራዊ እቅዶች የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ስምምነቱ እስከ እ.አ.አ 2028 እንደሚቆይ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የወርልድ ሪሶርስ ኢኒስቲትዩት እ.አ.አ በ1982 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርምር ተቋም ነው። ዋና ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ያደረገ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም