ፊላ -የዲራሼ ህዝብ ልዩ የኪነ-ጥበብ ውጤት

ፊላ - የዲራሼ  ህዝብ ልዩ የኪነ-ጥበብ ውጤት

ፊላ በቁጥር ከ24 - 32 በሚደርሱ በርዝመታቸዉ ከ5 - 100 ሴ.ሜ ሊደርሱ በሚችሉ የቀርከሃ እና የሸንበቆ ቁራጮች በአንድ በኩል ክፍት በአንድ በኩል ድፍን እንዲሆን ተደርጎ የሚሰራ የትንፋሽ የሙዚቃና የኪነት መሳሪያ ነው፡፡

የሙዚቃ መሳሪያ ነው ስንለው ድምጸቱና ቅላጼውን በመውሰድ ሲሆን የኪነት መሳሪያ የሚያሰኘው ደግሞ ከድምጸቱና ቅላጼው በሚወጣው ህብርና ልዩ ዜማ የሚከወን ምት/ዳንስ/ ስላለው ነው።

ፊላ የተለያዩ መጠን ያላቸው ከ24-32 በሚደርሱ በደረጃ በሚያድጉና በሦስት ቤዝ የተከፈሉ ቀርከሃና ሸንበቆዎችን በመንፋት የሚቀነባበር እጅግ ልዩና አስደማሚ ስልት ሲሆን በዘመናዊ አተያይ በመሳሪያ ብቻ የሚቀነባበር ሙዚቃ ነው፡፡

ይህ የሙዚቃ ሂደት በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ መሆኑና የድምጾቹን ፍሰት ተከትሎ ከላይ ወደ ታች የሚፈስ መሆኑ ከጃዝ የሙዚቃ ስልት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይሁን እንጂ ፊላ ከሙዚቃነቱ ወጥቶ በውዝዋዜ ነፍስ ሲዘራ መመልከት የጨዋታው ውቅር ነው፡፡ ተጨዋቾቹ ራሳቸው በ3- መሪዎች/ኮንዳክተር/ እየተመሩ ልዩ ውዝዋዜ ይከውናሉ፣ ኮንዳክተሮቹ/መሪዎቹ/ ራሳቸው ፊላ እየነፉ ወደ ውስጥ በመግባት ውዝዋዜውን ይመሩታል፡፡ እንደገናም ወደ ሙዚቃው ይመለሳሉ ፡፡ይህም በፊላ ውስጥ ራሱን የቻለ ምት፣ የሪትም አጠባበቅ፣ ቅብብሎሽ፣ ውህደት እና ሌሎች የማይገመቱ የውዝዋዜ ኩነቶች ይስተዋሉበታል።

ፊላ ከአንዷ የመጀመሪያ ወፍራም ድምጽ ከምታወጣው አሐድ ጀምሮ በጥልቀት ቅኝት እየተቃኘ ከ 24 እስከ 32 ቀጭን ቅኝት እስካለው ምት ሳይዛባ እንዲዘጋጅ የሚደረግ የሙዚቃ ጥበብ የሚገለጽበት መሳሪያ ነው፡፡

በዝግጅት ሂደት ውስጥ የፊላ ብዛት ካሳንታ/ቶንቶሊያ (ትልቁ ፊላ) ባለው ቁመት ተወስኖ እስከ ፊትንፊታያ ድረስ ብዙ ፊላዎች እንዲኖሩት ተደርጎ ይበጃል።

ፊላ ብቻውን ምሉዕነትን አይዝም የዲራሼ ባህል ታሪክ እና ጀግንነት ከፊላ ጨዋታ ጋር በአብሮነት የሚተየብ ሲሆን ጦር እና ጋሻ የፊላ አንድ አካል እየተደረገ በባህሉ ይዘወተራል ይህም ጀብድና ጀግንነትን የሚዘክር  ሌላኛው የፊላ ድምቀት ሎላታ ነው።

ሎላታ መሸጋገሪያ ሆኖ የሚያገለግል የፊላ ድምቀት ነው፣ በፊላ የሙዚቃ ጨዋታ የሎላታ መነፋት የጨዋታው ድምቀት ከፍ እያለ የመምጣቱ ምልከት ነው፣ በዚህ ወቅት ሴት የፊላ ተጫዋቾች እልልታ ሌላኛው ትንግርት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 

የሎላታ መነፋትን ተከትሎ ጋሻ እና ጦር የያዙ ተጨዋቾች ወደ መኃል ይገባሉ ጦር ይሰበቃል፤ በጋሻ ይመከታል ይህ ሲሆን የጨዋታው ድባብ ሌላ ድምቀት ያገኛል፡፡ የዲራሼ ሴቶች እልልታ የጨዋታው ልዩ ውበት ሆኖ ይስተዋላል ፣ሎላታ የመጨረሻው ምዕራፍ ማብሰሪያም ጭምር ነው ፡፡ተገልብጦ በቀጭኑ በኩል ወደ ውስጥ በመሳብ በሚወጣዉ ድምጽ የፊላ ጨዋታ ያበቃል፣ ሁሉም ተጨዋቾች ልዩ እና አስደማሚ ወደ ሆነው ዲታ/የእግር ምት ጭፈራ/ ይሸጋገራሉ።

የፊላ አመጣጥ ብዙ መላ ምቶችን የሚያስተናግድ በመሆኑ በእርግጠኝነት ፊላ የተጀመረበትን ሁኔታና ምክንያት ማስረዳት ከብዶ እናገኘዋለን ፡፡ይሁን እንጂ ከዲራሼ የዳማ ነገስታት ታሪክ ጋር የተሰሳረ ጉዞ እንዳለው በአፈ-ታሪኮች ይነገራል፡፡ ይህንን ተከትሎም ፊላ አሁንም በዲራሼ ማህበረሰብ የክብር እና የአክብሮት ጨዋታ ተደርጎ የሚሰድ ሲሆን ለዳማው፣ ሼላው እና ፖልዳው ያላቸውን አክብሮት የሚሳዩበትም ነው፡፡ 

ይህንን ምልከታ ተከትሎም ከቲቲባ ወገን የነበረው የመጀመሪያው ዳማ ወይም የዝናብ አባት እየተባለ የሚጠራው <<ፌላ>> ከተባለው ዳማ የሚያያዝ በተለይም ከሙዚቃ መውደዱና ለሙዚቃ ካለው ትልቅ ቦታ አንጻር የሚነገረው አፈ-ታሪክ ይገኝበታል ፡፡ሌሎች ከተፈጥሮ ጋር የሚያያዙ መነሾዎችም የሚነገሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በተለይም ከዝናብ ጠብታዎችና ›ሀሊላ› ተብሎ ከሚጠራው ክፍተት ያለው ተክል ጋር የሚያያዙ ንግርቶች ዋነኛዎቹ ናቸው።

ፊላ በልዩ ሁኔታ ከግብርና/እርሻ ሥራ ጋር ይተሳሰራል፡፡ ከግብርና ሥራ ጋር በሂደት እየዳበረ እንደመጣ የዲራሼ ህዝብ የግብርናና የእርሻ ባህልን ማስተዋል በቂ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተለይም ከግል የእርሻ ሥራ ወደ ጋራ የእርሻ ሥራ ምርትን ለማሳደግ የተመጣበትን መንገድና ከግል የሙዚቃ መሳሪያ <<ማይራ>> /ስድስት ባለደረጃና አጫጭር ቀጫጭን ሸንበቆ በጋራ ተሰናስሎ የሚገኝ የግል የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ/  በግል ከመጫወት ብቻ በሚል ተከፋፍሎ በጋራ ለመጫወት የተደረገውን ሽግግር ለፊላ አመጣጥ ታሪክ የሚያነሱ  ምሁራንና የታሪክ ነጋሪዎችም ይስተዋላሉ፡፡

በተለይም ከዲራሼ ህዝቦች የእርሻና የግብርና ታሪክ ጋር በተያያዘ የሚነሱ በጋራ የመስራት ልምዶች በዳኤታ(ከ2-7ሰዎች)፣ ኦርቶማ(ከደኤታ ከፍ ያለ ቁጥር)፣ እና ካላ(ደቦ) የሚባሉ አደረጃጀቶች በተለይም ከካላ (ደቦ- ከ20ሰዎች በላይ የሚሆኑ) ጋር የሚያያዝ ኩነት አለው።

በዲራሼ ማህበረሰብ ካላ የረዥም ታሪክ ባለቤት ነው፣ በካላ የሚፈጠር አብሮነትና መስተጋብር ለፊላ መፈጠር ተጠቃሽ ተደርጎ ይስተዋላል፡፡ በተለይም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፊላ መሰረት በመሆን ካላዎች እያገለገሉ መሆናቸው የዚህ ማሳያ ነው ፡፡ፊላ በደቦው/በካላ/ መሪ ካዳይት ቤት ነው የሚቀመጠው በዚሁ ምክንያት ፊላ ከካላ ጋር የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን፣ የፊላ ኦርኬስትራ ባንድ አድርጎ ካላን መጥቀስም ይቻላል።

የፊላ ጨዋታ በሥፋት የሚዘወተረው የእርሻ ሥራ ጋብ በሚልበት በወርሃ ጥር ወቅት ሲሆን የካላ ድግስ በየቦታው እየተዘጋጀ የፊላ ጨዋታ አብሮ በስፋት ይከወናል፡፡ ፊላ ከዲራሼዎች ህይወት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በፊላ ጨዋታ የጾታ የዕድሜ ልዩነት የለም የእኩልነት ተምሳሌት የሆነው የዲራሼ ማህበረሰብ በፊላ ይገለጻል ሴቶችና ወንዶች በእኩል የሚሳተፉበት ሲሆን በዚህም ዲራሼ እንደ ማህበረሰብ እኩልነትን ምን ያህል ከጥንት ይዞት እንደመጣና ዘመናዊ ማህበረሰብ እንደሆነ መመልከት ይቻላል።

የፊላ ጨዋታ በ2-ታላላቅ ወቅቶች ላይ በስፋት ይዘወተራል ፡፡ዲራሼዎች ዓመቱን ሙሉ በእርሻ ሥራ የሚጠመዱ ታታሪዎች ናቸው ፣በዓመት ሁለት ጊዜ ሰፊ ምርት ያመርታሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ያርፋሉ የራሳቸው የሆነና ከእርሻ ጋር የተያያዘ የቀን አቆጣጠር አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት አንጻራዊ በሆነ መልኩ የእርሻ ሥራ ጋብ በሚልበት ወቅት የእረፍት ጊዜ ይኖራቸዋል። 

የመጀመሪያው የእረፍት ወቅት ከነሐሴ መጨረሻ አንስቶ መስከረምን ያጠቃልላል ፡፡ይህም ዋናው የበልግ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ ሲሆን ላኮታ ይባላል ፡፡ላኮታ ማለት እንኳን ከአስቸጋሪው የዝናብ፣ የመብረቅና የጎርፍ ወቅት በሰላም ወጣችሁ የሚለውን ይወክላል፣ በዚህ ወቅትም ደማቅ የፊላ ጨዋታ ይከወናል፡፡ የካላ ቡድኖች ከየቤተሰቡ ምግብና መጠጥ በማሰብሰብ /ፖሃና/ መጠነኛ ድግስ አዘጋጅተው ፊላ የሚጫወቱበት ወቅት ነው፡፡በተለይም ከእንቁጣጣሽና /አዲስ ዘመን/ እና መስቀል በዓል ጋር ተደምሮ በስፋት ይከበራል።

ሁለተኛው የዕረፍት ወቅትና ዋናው የፊላ ጨዋታ ወቅት ከጥር መጀመሪያ አንስቶ እስከ የካቲት ሲሆን የሃጋይት/ሀገያ/ ምርት ተሰብስቦ ወደ ማከማቻው ፖሎታ/የእህል ጉድጓድ የሚገባበትና በዲራሼ ማህበረሰብ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የሆነው ታላቁ ዝናብ/ ካሻኔ-ካልካሎ/ እስኪመጣ ድረስ ነው ይህ ወቅት የእረፍት፣ የጥጋብና የመዝናናት ወቅት በመሆን ሃይሶት/እረፍት/ ይባላል። 

በዚህ ወቅትም በጋርዱላ ዞን የሚገኙ ህብረ-ብሔራዊ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ ሀይሶት-ህርባ ይከበራል ፡፡የዓመቱ መጀመሪያ ወራቸውን አንድ ብለው /ካልካሎ-የካቲት/ ከመቁጠራቸው በፊት የአዲስ ዓመት መግቢያን የሚያከብሩበት ወቅት ነው ፡፡ህዝቡ ከዓመታዊ የእርሻ ሥራ ማረፉን ጊዜው የደስታ፣ የሰርግ፣ የጨዋታና የመዝናናት መሆኑን አመላካች ነው፣ በዚህ ወቅት ፊላ እና ድግስ በየቦታው አይጠፉም፡፡ ፓርሾታ/ቦርዴ-ጨቃ/ በየቦታው ይጠመቃል፤ ሰንጋ ይጣላል በየቦታው ድግስ ይደገሳል፤ ድግሱ በዲራሼዎች ፊላ ይደምቃል የፊላ ጨዋታ የዲራሼዎች ባህል ዋነኛ መገለጫ ነው።

The contribution of Ethiopia to the science of Jazz by the Derashe በዶ/ር ሙላቱ አስታጥቄ በፈረንጆቹ 2019 ገና በእስራኤል የቀረበ የኮንሰርት መጠሪያ ሲሆን በተለይም ባለ 7-ኖታው ፊላ ልዩነቱን የሚገልጽና ለጃዝ ሙዚቃ እንደ ፈር ቀዳጅ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንና ዲራሼዎች የሙዚቃ ባለቤቶች መሆናቸውን ያስመሰከረ ልዩ ጥበብ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም