ለሌማት ትሩፋት ትልቅ አቅም የሆነው የመምህሩ የዶሮ ቤት ፈጠራ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ ለሌማት ትሩፋት ትልቅ አቅም የሆነው የመምህሩ አዲስ የዶሮ ቤት ፈጠራ ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሃላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ ነዋሪ የሆኑት መምህር ስምዖን አጭሶ በአጎራባች ዞኖችና ከተሞችም ጭምር በስራቸው ይታወቃሉ።

የአራት ልጆች አባት የሆኑት መምህር ስምዖን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል።

በሰሩባቸው አካባቢዎችም ትምህርት ቤት ማሰራትን ጨምሮ በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች በጎ አሻራቸውን ያሳረፉ አንጋፋ መምህር በመሆናቸው በነዋሪዎችና በትምህርት ማህበረሰቡ ዘንድ ከበሬታ አትርፈዋል።

በሃላባና አካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በልዩ የፈጠራ ስራቸው በሚታወቁበት ''የዶሮ ቤት አናጢው መምህር'' በመባል ብዙዎች የሚያውቋቸው መምህር ናቸው።

በተለይ "ፊዚክስና ሂሳብ ከልብ እወዳለሁ'' የሚሉት መምህር ስምዖን፤ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል።


 

በ300 ካሬ ሜትር መኖሪያ ግቢያቸው ጥቂት ዶሮዎችን ማርባት ሲጀምሩም ምቹ ሁኔታ ባለማየታቸው አካባቢ የማይበክል ለባክቴሪያ የማይጋለጥና ለጥበቃና ለአረባብ ምቹና ቀላል አሰራርን ለመከተል ዘየዱ።

በዚህም መሰረት ''የዶሮ ቤት አናጢው" አዲስ የዶሮ ቤት ሰርተው ጥቅም ላይ በመዋሉ የበርካቶችን ቀልብ ገዝቶ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሌማት ትሩፋት ትልቅ አቅም የሆነው የመምህሩ የዶሮ ቤት በርካቶች ገዝተው እየተጠቀሙበት ለመምህሩም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኗል። 

"የዶሮ ቤት ፈጠራዬን በሳይንሳዊ ልኬት ለመስራት የፊዚክስ ዕውቀቴ ጠቅሞኛል"' ሲሉም መምህር ስምዖን ይናገራሉ።

የመምህር ስምዖን ፈጠራ ኬጂ ዶሮዎችን በቀላሉ ለመንከባከብ፣ ሲታመሙም ለመከታተል እንዲሁም ከአደጋ ለመጠበቅና ጽዱ ግቢ እንዲኖር በማስቻሉ በደንበኞች ዘንድ ተመራጭ አድርጎላቸዋል።

ለፈጠራ ስራቸው የባለቤትነት መብት እስካሁን ባያገኙም ለሌሎች ወጣቶች ልምዳቸውን በማጋራት እንዲሰሩ ከማድረግ ባሻገር በዶሮና እንቁላል እንዴት ምርታማ መሆን እንደሚቻል የነጻ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ። 


 

መምህሩ የዶሮ ቤት በመስራት ብቻ ሳይሆን ከ90 በላይ ዶሮዎችን በአነስተኛ ግቢያቸው በማርባትም ኪሳቸውንም ሌማታቸውንም መሙላት ችለዋል።

በጠባብ ጓሮ ከሚያረቧቸው ዶሮዎችም እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል።

''እንደ ሀገር የዶሮ ስጋና እንቁላል አጠቃቀም በጣም አነስተኛ ነው'' የሚሉት መምህር ስምዖን፤ የሌማት ቱርፋት መርሀ ግብር ተግባራዊ መደረጉ ለዚህ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የእርሳቸው የፈጠራ ውጤት ደግሞ የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ በየግቢው ዶሮ በቀላሉ በማርባት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ብሎም ተጨማሪ ገቢ እንዲያመነጩ በማድረግ ለመርሀ ግብር ስኬት ያግዛል የሚል እምነት አላቸው።

ከ20 እስከ 100 ዶሮዎችን የሚይዙ ኬጂዎችን የሚሰሩት መምህር ስምኦን አሁን ከክልሉ ውጭ ያሉ ሰዎችም ምርታቸውን ለመግዛት እየጠየቁ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛም ሆነ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ዕንቁላል ከውጭ ከመግዛት በራስ በቀላሉ አርብቶ መጠቀም እና የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንደሚችልም ይመክራሉ።


 

''አሁን ወደ ጡረታ ተጠግቻለሁ'' የሚሉት መምህር ስምዖን፤የጀመሩትን የዶሮ ቤት ስራ እና የዶሮ እርባታቸውን በማስፋት በሙሉ ጊዜ ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

የእስካሁን ስራቸውን በአነስተኛ መኖሪያ ግቢያቸው እያከናወኑ በመሆኑ ቀጣይ ዕቅዳቸው ዕውን በማድረግ ማህበረሰቡን ተደራሽ ለማድረግ የመስሪያ ቦታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም  በመንግስት በኩል ቢደገፉና የመስሪያ ቦታ ውስንነት እና ተያያዥ ችግሮች ቢፈቱላቸው አሁንም ከአካባቢያቸው አልፈው እንደ ሀገር ተምሳሌት የመሆን ህልም እንዳላቸው ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም