የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር የአባላትንና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር የአባላትንና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጠናከር የአባላትንና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት ከተጀመረ ከ 50 አመት በላይ እንዳስቆጠረ ይታወቃል፡፡
አሁን ላይ በአገሪቱ የተደራጁ የተለያዩ የህብረት ስራ ማህበራት በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ይህን ተከትሎ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን በህብረት ስራ ዘርፍ የካበተ ልምድ ካላቸው ሀገራት ልምድ በመቅሰምና በመቀመር በከተማዋ ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሞክሮውን እያጋራ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ለ10 ቀናት በኔዘርላንድ ያደረገውን የህብረት ስራ ጉብኝት እና የልምድ ልውውጥ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በኔዘርላንድ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ልእልቲ ግደይ ገልጸዋል፡፡
ማህበራቱ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ በመሳተፍ ሀገሪቱ የተሻለ እድገት እንዲኖራት ማስቻላቸውን በጉብኝታቸው መመልከታቸውን አንስተዋል፡፡
በኔዘርላንድ የሚገኙ ማህበራት የሚያመርቷቸውን ምርቶች ከራሳቸው ባለፈ ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ለሀገራቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ በበኩላቸው ፤የህብረት ስራ ማህበራት የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር ራሳቸውን በተሻለ ደረጃ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
የህብረት ስራ ማህበራት የሀገር ኢኮኖሚን በማሳደግ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ያደጉ አገራትን ተሞክሮ መተግበር እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የህብረት ስራ ማህበራት ተወካዮች በበኩላቸው ፤ውይይቱ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ያላቸውን አቅም በመፈተሽ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ የሚያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በመዲናዋ ከ9 ሺህ 800 በላይ ህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።