ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥና የዲጂታል ግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር ትፈልጋለች-አምባሳደር ካንግ ጁንግ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥና የዲጂታል ግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር ትፈልጋለች-አምባሳደር ካንግ ጁንግ
አዲስ አበባ፤ህዳር 9/2017 (ኢዜአ)፦ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት፣ የንግድ ልውውጥና ዲጂታል የግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ ተናገሩ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፥ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደርን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚህም ወቅት፥በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣በኢንቨትመንትና በንግድ ልውውጥ ያለውን ግንኙነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ታሪካዊ ነው ብለዋል።
አክለውም፥በኮሪያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች የኮሪያን ህዝብ በመወገን ተዋግተው የደም ዋጋ የከፈሉ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የቡናና የቅባት እህል ወጪ ምርቶችን ወደ ኮሪያ ሪፐብሊክ ገበያ እንደምትልክ ገልጸው፥ ኢትዮጵያ ከኮሪያ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት አማራጮችንና ዕድሎች ለአምባሳደሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱ ባለሀብቶች ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችን ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወሰደችው አገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ፈጣን እድገት ማስመዝገቡን የገለጹት ሚኒስትሩ የኮሪያ ሪፐብሊክ በዲጂታል ንግድና ግብይት ልምድ ያላት ሀገር በመሆኗ በኢኮሜርስና ዲጂታል ዘርፍ አቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ ድጋፍ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ካንግ ጁንግ፥ኮሪያ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨትመንት፣ የንግድ ልውውጥና ዲጂታል የግብይት ሥርዓት መደገፍና ማጠናከር እንደምትፈልግ መናገራቸውን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።