ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት በፀጥታና ፍትህ ዘርፍ በተደረጉ ማሻሻያዎች ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 9/2017(ኢዜአ):- በለውጡ ዓመታት በፀጥታና ፍትህ ዘርፍ በተደረጉ ማሻሻያዎች ትላልቅ ወንጀሎችን በመመርመር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከፍትሕ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያስላሴ ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ሚኒስትሯን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት በፀጥታና ፍትህ ዘርፍ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት በመስራት ትላልቅ ወንጀሎችን በመመርመር ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።


 

በሪፎርሙ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተከናወኑ ስራዎች በተለይ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በሎጂስቲክስ አቅም ፣በቴክኖሎጂ፣ በአደረጃጀት፣ በወንጀል መከላከልና ምርመራ፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በፖሊስ ለፖሊስ የውጭ ግንኙነት ጠንካራ አቅም መፈጠሩን አመልክተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያስላሴ በበኩላቸው የፍትህ ዘርፍ ፎረምን በማጠናከር ተደራሽነትን ለማስፋት በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ሚኒስትሯ በወንጀል መከላከል እና በወንጀል ምርመራ የተፈጠሩ የፖሊስ አቅሞችን መጎብኘታቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም