ዘወትር ሰኞ የምናደርገውን የውይይት ፕሮግራም የሄድንበትን የ52 ሳምንታት ቆይታችንን ጥንካሬ እና ድክመት ለይተን ወደ ሌሎች ቢሮዎቻችን የምናስፋፋው ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ዘወትር ሰኞ የምናደርገውን የውይይት ፕሮግራም የሄድንበትን የ52 ሳምንታት ቆይታችንን ጥንካሬ እና ድክመት ለይተን ወደ ሌሎች ቢሮዎቻችን የምናስፋፋው ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ “ወርቃማዋ ሰኞ” ብለን ዘወትር ሰኞ የምናደርገውን የውይይት ፕሮግራም የሄድንበትን የ52 ሳምንታት ቆይታችንን ጥንካሬ እና ድክመት ለይተን ወደ ሌሎች ቢሮዎቻችን የምናስፋፋው ይሆናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት በከንቲባ ጽህፈት ቤት እና በጊቢ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ጋር በመሆን “ወርቃማዋ ሰኞ” ብለን ዘወትር ሰኞ የምናደርገውን የውይይት ፕሮግራም አንደኛ ዓመት ዛሬ ማለዳ አክብረናል ብለዋል።
እነሱ ጨለማው ሰኞ (Black Monday ) የሚሉትን እኛ ወርቃማው ሰኞ ብለን ላለፉት 52 ሳምንታት ከጥዋቱ 2 እስከ 3 ሰአት ባለው ጊዜ የከንቲባ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የኮሙዩኒኬሽን እና የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በጋራ በመሆን በየሳምንቱ ከሰራተኞቻችን ጋር እንደቤተሰብ እየተማማርን እና እየተመካከርን ሳምንቱ ሙሉ ወርቃማ እንዲሆንልን መልካም ምኞት ተለዋውጠን አብረን ቡና ጠጥተን ስራችንን እንጀምራለን ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንን የምናደርገው የበለጠ ለተገልጋዮች ቅርብ ለመሆን እና አገልግሎታችንን ለማሻሻል እርስ በእርሳችን የምንመካከርበት፣ የምንማማርበት፣ ልምድ የምንለዋወጥበት እንዲሁም እንደ መሪ ታች ካሉ ሰራተኞቻችን ጋር ጭምር ማህበራዊ ህይወታችንን ከስራችን ጋር በማስተሳሰር ለመቀራረብ እና ሃሳብ ለመለዋወጥ ሲሆን በዚህ ሁኔታ 52 ሳምንታትን አሳልፈናል ሲሉም ጠቅሰዋል።
በዛሬው ፕሮግራማችን ደግሞ ዶክተር ምህረት ደበበ ስለ ስራ እና ህይወት (work and life balance) ሚዛን መጠበቅ ትምህርት አካፍለውናል ብለዋል።
ፕሮግራሙ በከንቲባ ጽህፈት ቤት ይጀምር እንጂ ወደ ሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት እና መስሪያ ቤቶች የሚሰፋ ሲሆን እስከ አሁን የሄድንበትን የ52 ሳምንታት ቆይታችንን ጥንካሬ እና ድክመት ለይተን ወደ ሌሎች ቢሮዎቻችን የምናስፋፋው ይሆናል ሲሉም አመላክተዋል።