ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመረጠች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር መምከራቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኮፕ 29 ዓለም አቀፍ ጉባዔ እየተካሄደ ባለው የአዘርባጃን ባኩ መድረክ ጎን ለጎን የተካሄደው የስራ ኃላፊዎቹ ውይይት የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመመከት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ስለሚወጣው በጎ ሚና ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።


 

በዚህ ረገድ ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) እያደረገ ላለው ተሳትፎ ሚኒስትር ዴዔታው አመስግነዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የአየር ንብረት ተፅዕኖ ለመከላከል ድጋፍ ለማድረግ በሀገራት መካከል ትብብር እንዲጎለብት የማድረግ ተልዕኮ ያለው የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ኢትዮጵያ መመረጧ ተመለክቷል።

ውሳኔው ኢትዮጵያ በዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲጎለብት እየተወጣች ላለው ጉልህ ሚና ዕውቅና የሰጠ ሆኗል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ስዩም መኮንን ከዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር ባደረጉት ምክክር በዘላቂ የልማት ዕቅዶች ውስጥ የጅምር ፈጠራ ሀሳቦች(startups) ሚናን ማላቅ እንዲሁም ለአካታች የኢኮኖሚ ሽግግር ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያም መክረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ጥረት የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ሚኒስትር ዴዔታው አረጋግጠዋል።

አለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ትብብር(P4G) እ.አ.አ 2017 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ዴንማርክ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሜክሲኮ እና ቬትናም መንግሥታት የተመሰረተ አጋርነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም