የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የበለጠ እንዲቀራረቡና ኅብረብሔራዊ አንድነታቸው እንዲጠናከር ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የበለጠ እንዲቀራረቡና ኅብረብሔራዊ አንድነታቸው እንዲጠናከር ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2017ኢዜአ)፦የብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን የበለጠ እንዲቀራረቡና ኅብረብሔራዊ አንድነታቸው እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን የጋርዱላ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብርሀኑ ኩናሎ ገለጹ።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል።
ይህን ተከትሎ ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የበዓሉን የዝግጅት ስራዎች ለመመልከት አርባ ምንጭ ከተማ ገብተዋል።
የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተደረገ ባለው የመገናኛ ብዙሀን ጉብኝት የጋርዱላ ዞን አጠቃላይ የልማት ስራዎች ጎብኝተዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋርዱላ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብርሀኑ ኩናሎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ወንድማማችነት እና እህትማማችነት የሚጎለብትበት ነው፡፡
መተሳሰብ እና አብሮነት የሚጎላበት እንዲሁም ብሔር ብሔረሰቦች እሴቶቻቸውን እና ባህሎቻቸውን የሚያሳድጉበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ አራት ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው እነኝህም ዲራሼ፣ ኩሱሜ፣ ማሾሌና ሞሲዬ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የጋርዱላ ዞን ነዋሪ ያቀረበው የመዋቅር ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ በከፍተኛ ደስታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ብሔረሰቦቹ ጥንትም አብረው የኖሩ ፣አሁንም ነገም አብረው የሚኖሩ የተጋመዱ ህዝቦች መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው አንስተዋል፡፡
ዞኑ ከተዋቀረ በኋላ የተለያዩ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
የጋርዱላ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ ዘሪሁን ግንባሬ ዞኑ ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዞኑ ታታሪ ህብረተሰብ ያለበት መሆኑን ገልጸው፥ ነዋሪው በተቀረጹ ኢኒሼቲቮች አማካይነት ምርቱን በስፋት እያሳደገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።