ቀጥታ፡

በክልሉ ለእርሻ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ስልጠና ተሰጠ

መቀለ፤ ህዳር 8/2017 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል ለእርሻ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

ስልጠናውን የሰጡት  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢያሱ አብረሃ እደገለጹት የግብርና የማስፈፀም አቅም ለማሳደግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማወቅና በተከታታይ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል።

የሀገሪቱ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መትጋት እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

"ለዚህም  አስቻይ ሁኔታ መፍጠር አለብን "ያሉት ዶክተር ኢያሱ፣ በተለይ በክልሉ የግብርና  አሠራሮችን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል በኩታገጠም ማምረት፣ የመካናዜሽን እርሻና  የመስኖ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት እንዲሁም ምርታማነትንና የገበያ ተደራሽነትን ማሳደግ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በስንዴና ገብስ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመላክተዋል።

"አርሶ አደሩን በቅርበት የሚያገለግለው  የግብርናው ባለሙያ በመሆኑ ሀገራዊ ፖሊሲው ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጥ መደረጉ ወሳኝ ነው" ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምስራቃዊ ዞን የፃዕዳ እምባ ወረዳ የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ አብሪሃ ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

 

 

 ።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም