ቀጥታ፡

በድሬደዋ ከነገ ጀምሮ የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ይሰጣል

ድሬደዋ ፤ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ በድሬደዋ አስተዳደር ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው ታዳጊ ሴቶች የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት እንደሚሰጥ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ነገ በሚጀመረውና ለአምስት ቀናት በሚቆየው የክትባት ዘመቻ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ፤ በተለያዩ ጊዜያት በየደረጃው ለሚገኙ ታዳጊ ሴቶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንነትና ሊያስከትል የሚችለው የጤና ችግር ላይ ያተኮረ ግንዛቤ መሰጠቱን አስታውሰዋል።


 

ከነገ ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆናቸው ታዳጊ ሴቶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር የመከላከያ ክትባት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ከነገ ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎችና በጊዜያዊ ክትባት መስጫ ማዕከላት 30 ሺህ የሚጠጉ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ለክትባት ዘመቻው አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን በማስታወስ።

በመሆኑም ለክትባት ዘመቻ መሳካት ወላጆች፣ አሳዳጊዎች እንዲሁም መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች ታዳጊ ሴቶች የመከላከያውን ክትባት እንዲወስዱ የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም