ቀጥታ፡

የጎንደር ማተሚያ ድርጅት ያስገነባውን ህንፃ አስመረቀ

ጎንደር፤ ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ የጎንደር ማተሚያ ድርጅት በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን ህንጻ ዛሬ አስመረቀ፡፡

ማተሚያ ድርጅቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉንም አክብሯል፡፡

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ መስፍን እንደተናገሩት፤ ማተሚያ ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት የህትመት ጥራትና ተወዳዳሪነቱን በማሳደግ ፈር ቀዳጅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡


 

ድርጅቱ አሁን ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በ215 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ወደ ህትመት ኢንዱስትሪው የተቀላቀለው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ጠቅሰው፤ 32 ዘመናዊ የህትመት ማሽኖች እንዳሉትም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለ173 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

"ድርጅትቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በህትመት ኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ የሚያስችለውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በማዘጋጀት በቅርቡ ወደ ትግበራ ይገባል" ብለዋል።

ማተሚያ ድርጅቱ በ40 ሚሊዮብ ብር ወጪ ያስገነባው አዲሱ ህንጻ ለህትመት ስራዎች፣ ለምርት ማከማቻና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

''የጎንደር ማተሚያ ድርጅት በሀገሪቱ የህትመት ታሪክ የራሱን ደማቅና ጉልህ አሻራ ያሳረፈ አንጋፋ የህትመት ተቋም ነው'' ያሉት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡


 

የሰራተኞችን ምርታማነት በመገንባትና የተቋም የባለቤትነት ስሜት እንዲያዳብሩ በማድረግ ዘመናትን በውጤታማነትና በተወዳዳሪነት የተሻገረ የህትመት ተቋም እንደሆነም አመልክተዋል፡፡  

ከተማ አስተዳደሩ የተቋሙ ራዕይ እንዲሳካና ለከተማውም ሆነ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን ማህበራዊ አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በድርጅቱ በምርጥ ፈጻሚነት እውቅና የተሰጣቸው አቶ ውባንተ ሃይሉ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ተወዳዳሪ አንዲሆን በተመደቡበት የሙያ ዘርፍ ሚናቸውን መወጣት እንደቻሉ ገልፀዋል።

ማተሚያ ድርጅቱ 50ኛ ዓመቱን የወርቅ እዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በጡረታ ለተሰናበቱና በስራ አፈጻጸማቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰራተኞች የእውቅናና ምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡

በማተሚያ ድርጅቱ አዲሱ የህንጻ የምረቃ ስነ ስርአት ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የማተሚያ ድርጅቱ ሰራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም