በባህር ዳር ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ሌት ከቀን እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ሌት ከቀን እየተከናወኑ ነው
ባህር ዳር፤ ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ሌት ከቀን እየተከናወኑ መሆናቸውን ከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው አስታወቁ።
“የሀሳብ ልእልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ምስረታ በፓናል ውይይትና ሌሎች ዝግጅቶች በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የብልጽግና ፓርቲ ብዝሃ ኢኮኖሚ ላይ በማተኮር ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
''ፓርትው በአገራችን ለዓመታት ተጀምረው የቆሙ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለአገር እድገትና ለህዝብ ተጠቃሚነት እያዋለ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶችን በመጀመርና በጥራት ፈጥኖ በማጠናቀቅ በኩል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ፓርቲ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በባህር ዳር ከተማም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች ሌት ከቀን እየተከናወኑ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለዚህም የህዝቡ ሙሉ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን የሚያስተሳስር የልማትና የፖለቲካ አቅጣጫ በመቅረጽ ለህዝብ ተጠቃሚነት የሚተጋ ፓርቲ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞላ ሁሴን ናቸው።
ብልጽግና ዘመን ተሻጋሪ እሳቤዎችና ተግባረት ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመው ፓርቲው የተዛቡ ትርክቶችን በማረምና ለሃገረ መንግስት ግንባታ ተግቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
''በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጽናት ታግሎ የሚሻገር፣ ፈተናን ወደ እድል የመቀየር ልምድን ያጎለበተና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚታገል ፓርቲ መሆኑን ያስመሰከረ ነው'' ብለዋል።
የፓርቲውን 5ኛ ዓመት በዓል ሲከበርም እስካሁን የተመዘገቡ ድሎችን በማጽናት፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ እንደሆነም ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ በተከበረው የምስረታ በዓል ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት፣ የፓርቲው አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።