ጊዶሌ በህብረ-ዜማ የደመቀች፤ በኪነ-ጥበብና በታሪክ ያበበች ከተማ

ጊዶሌ በህብረ-ዜማ የደመቀች፤ በኪነ-ጥበብና በታሪክ ያበበች ከተማ፡፡

ከርዕሰ መዲናችን አዲስ አበባ በስተ-ደቡብ አቅጣጫ በ525 ኪሎ ሜትር፣ ከአርባ ምንጭ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ነች። ከተማዋ በፀሀይ መውጫ በኩል የጫሞ ሀይቅና የነጭ ሳር ሰንሰለታማ ተራሮችን ተንተርሳ ተመሥርታለች፡፡ 

የጊዶሌ ከተማ ገጽታ


 

የቀድሞ ጋርዱላ የአሁኗ ጊዶሌ ከተማ አመሠራረት የሚጀምረው የአጼ ምኒልክ ጦርን ይመሩ የነበሩት ደጃች አመነ እና ደጃች ገነሜ የተባሉ መሪዎች በጋርዱላ ተራራ በ1883 ዓ.ም በሠፈሩ ጊዜ ሲሆን በወቅቱ እስከ ቦረና ያለውን አካባቢም በማዕከላዊነት እንዳገለገለች ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ዳግማዊ አጼ-ምኒልክ ከሶማሊያ እስከ ሱዳን የሚዘልቀውን ደቡባዊ የሀገራችንን ድንበር በወቅቱ የኬኒያ ቅኝ ገዢ ከነበረችው እንግሊዝ ጋር የተካለሉት በጋርዱላ ከተማ እንደሆነና የእንግሊዝ ቆንስላ ጽ/ቤትም እስከ 1929 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ ድረስ በጋርዱላ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

የእንግሊዝ ቆንስላ በጋርዱላ

በጊዜው የመንግሥት የአስተዳደር ማዕከል ሆና ስታገለግል የነበረችው ጋርዱላ የአርበኞች የስንቅና የመረጃ ምንጭ ነች በሚል በ1929ዓ.ም በጣሊያን ወራሪ ኃይል የአውሮፕላን ድብደባ ሠለባ ሆናለች፡፡ 


 

ከዚህ በኋላ ከተማዋ ከጋርዱላ በስተ-ምስራቅ በሚገኘው ዝቅተኛ ቦታ ላይ እንድትቆረቆር አድርጓታል፡፡

በዘመኑ የቀጠናው የትምህርት፤ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትሥሥር ማዕከል በመሆንም አገልግላለች፡፡

ጊዶሌ በህብረ-ዜማ የደመቀች፤ በኪነ-ጥበብና በታሪክ ያበበች ከተማ ናት፡፡

በዓለም ብቸኛው ባለ-ብዙ (ሰባት) ኖታ ፊላ የትንፋሽ መሳሪያ የሙዚቃ ጨዋታ የጊዶሌ ከተማ ድምቀት ነው ፣ ፊላ-የምድሪቱ ልዩ ጣዕም ነው፣ ጊዶሌ ደግሞ ጥዑም ዜማ የሚደመጥባት ምድር ናት፡፡

ሺዋ፣ ሌኦታ እና ሌሎች ባህላዊ ጨዋታዎች የከተማዋ ውበት ናቸው፡፡

ጊዶሌ ሲመጡ የአድዋን ታሪክ በአካል ይዳስሳሉ፣ አድዋ ዘማቹን የጋርዱላ ጊዮርጊስን ከታሪክ ማህደሩ ጋር ፤ ትንታግ የነበሩና ፋሽስትን ሠላም የነሱ የአርበኞች መታሰቢያ መቃብርን ከዝክሩ ጋር፤ የእንግሊዝ ቆንስላን ከትውስታው ጋር፤ የአርበኞች ዋሻን ከግርማ ሞገሱ ጋር፤ ኢትዮጲያዊነትን ከህዝቡ ጋር ተዋህዶ ያገኙታል፡፡

ኪነ-ጥበብ፣ ልዩ ባህል እና እሴትን ተነግሮ በማያልቅ ልክ ይዳስሱታል፤ የፍርድና የዳኝነት ሥርዓቱ፣ የሰርግና የልቅሶ ሥርዓቱ ከታሪክ ማህደር ተሰናስሎ የተከተበበት ምድር ብቻውንም ታሪክ አስረጂ ነው፡፡

ተዓምረኛው የጋርዱላ ሞሪንጋ

ተዓምረኛው ሞሪንጋ መነሻውና የመጀመሪያ ግንዱን በአካል ያዩታል፤ በኩርኩፋና በፎሰሴ ምግብ ጣዕም ይደመማሉ፤ ጨቃ እና መና ጠጥተው ይረካሉ፤ በጋርዱላ ከባህል መድኃኒቶቿና ከፈዋሽ ተፈጥሮዋ፣  ከምንጮቿና ከወንዞቿ እርካታን ይጎናጸፋሉ፡፡


 

በሸንጎዎቿ ዙሪያ ተቀምጠው እንደ ጥንታዊያን ጥበብንና እውቀትን ከታላላቆች ይማሩበታል ህግ ፣ሥርዓትንና አስተዳደርን ከጥንት ትውፊት ያገኙበታል፡ የንግስና ሥርዓትንና የታሪክ ቅብብሎሽን ባማረ አንደበት ሲተረክ ያገኙታል፣ እነኚህን ሁሉ በጊዶሌ በአንድ ተሰናስለው ያገኟቸዋል፡፡

ጊዶሌ ከጋርዱላ ተራራ ግርጌ እንደመቆርቆሯ የጋርዱላ ተራራ ግርጌ በነፋሻማ አየሯ መንፈስን ያድሳል ለሽርሽር-ሀይኪንግ (hiking)፣ ለፊልምና ለፎቶ መሳጭ በሆነው ጋርዱላ የማይዘነጉ ምስሎችን ይከትባሉ፡፡

ጊዶሌ ከለውጡ ማግስት የተስፋና የብልጽግና ማዕከል ሆናለች፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በ2022 ጊዶሌ ከተማ ሁለንተናዊ ብልጽግና ያስመዘገበች ከተማ እንድትሆን ራዕይና ትልም በመያዝ መጠነ ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡

የከተማዋ ሌላኛው ገጽታ

በከተማዋ መጠነ ሰፊ ጅምር ሥራዎች ይገኛሉ ፡፡ከተማዋ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለፕሮጀክቶችና ለመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዲውል በመመደብ ውበቷን እያጎላች ትገኛለች፡፡

ከተማዋ የጋርዱላ ዞን የኢኮኖሚ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን አሁን ላይ በከተማዋ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ናቸው፡፡


 

የከተማዋ የውስጥ ገቢ በ2011ዓ.ም ከነበረበት ፈጣን ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡

የከተማው ስትራቴጂክ ፕላን የከተማዋን ብልጽግና በሚያሳካ መልኩ የ30፣ 30 እና 40 ምጣኔ መርህን በተከተለ መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡ የካዳስተርና የዲጅታል ፋይል ማኔጅመንት ሥራዎች ከተማዋን በቀጣይ ስማርት ለማድረግ በተያዘው ዕቅድ በጥሩ ጅምር ላይ ይገኛሉ፡፡

በውስጥ ገቢ የተሰራ ግንባታ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልልቅ ግንባታዎች በከተማዋ እየለሙ ነው፤ በመንገድ ሽፋን ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ውስጥ ለውስጥና ከውጪ መዋቅሮች ጋር ተሳስራለች ፣በመንገድ ሥራ 67.5 ኪ.ሜ ሽፋን አላት፡፡

የውሃ መስመር ዝርጋታ በከተማዋ 30 ኪ.ሜ ላይ ደርሷል ፡፡80 በመቶ የሚጠጋው የከተማው ማህበረሰብ የመብራት አገልግሎት በቆጣሪ ተጠቃሚ ነው፡፡ በከተማዋ የዘመናዊ ቄራ እና መናኽሪያ አገልግሎት ውጤታማ ሥራ ተሠርቶበታል፡፡ 

የሥራ-ዕድል ፈጠራ በልዩነት የከተማዋ አጀንዳ ተደርጎ እየተመራ ይገኛልሸ፡

በግብርናና በሌማት ትሩፋት የሚሰራው ሥራ ከተማዋ የምግብ ዋስትና ፍላጎቷን በራሷ እንድትሸፍን መሠረት ጥለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ ከ200,000 በላይ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የተዳቀሉ ዘመናዊ ችግኞች ለማህበረሰቡ ያሰራጫል፡፡

በዚህም በከተማው ከ44,046 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ፡፡በቤቶች ልማት በመኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማኅበራት በከተማዋ 22 ቤቶች እንዲሁም በመንግስት 228 የቀበሌ ቁጠባ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

ከተማዋ በጥንካሬና በልዩ የእርሻ ጥበብ ዙሪያውን የሚመግቡ የደራሼ፤ የኩሱሜ፤ የማሾሌና የሞስዬ ብሔረሰብ አርሶ-አደሮች የንግድ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን በነጭ-ልዩ ማኛ ጤፍ፣ በማሽላ፣ በበቆሎ፣ በራራ፣ ቆኖዳ፣ ኬራያ፣ ቦሎቄ፤ ባቄላ፣ አተር፣ ማሾ፣ ዘንጋዳ፣ ዲሽከሮ፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ሌሎች ሰፊ የብርዕና ጥራጥሬ ምርቶች ትታወቃለች፡፡

ቡላ፣ ቆጮ፣ ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ቀይስር፣ ድንችና ሌሎች አትክልቶችና የአትክልት ውጤቶች የከተማዋ መገለጫ ናቸው፡፡

የደራሼዎች የእርሻ ዘዴና ጥበብ ለዓለም በተሞክሮነት የሚቀርብ ነው፡፡

ደራሼዎች በዓመት ሁለት ሦስቴ ሰፊ ምርት የሚያመርቱ ጠንካራና ታታሪ ህዝቦች ሲሆኑ ታርጋና ፖታያ የደራሼ ብሔረሰብ የአፈርና ውሃ እቀባ ተሞክሮን የሚያሳዩ ስራዎች ናቸው ፡፡

ደራሼዎች ያመረቱትን ምርት በመሬት ውስጥ ተቆፍሮ በሚዘጋጅ ፖሎታ ተብሎ በሚጠራ ጎተራ ለዓመታት ያቆያሉ ለዚህም ጋርዱላ የረሀብ ዱላ ተብላለች፡፡ 

  በከተማዋ ዓለም-አቀፍ፤ ሀገር-አቀፍና አካባቢያዊ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ፡፡

የእንግሊዝ ቆንስላ ቦታ፣ ጣሊያንን ድል የነሱ የአርበኞች ሐውልት፣ በሽልማት ለአድዋ ዘማቾች የተበረከተው የጋርዱላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላት፤ ፊላ፣ የጋርዱላ ጥብቅ ደን፤ የጋርዱላ የአርበኞች ዋሻ፤ የእርከን ሥራ፤ ታርጋና ፖታያ፤ ሞሪንጋ፤ ፖሎታ፣ ሞራ/ሸንጎ/ እና መሠል ቅርሶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በከተማው 14.15 ሄክታር መሬት በተለያዩ አገልግሎቶች ለምቷል በቀጣይ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስክ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችና አልሚዎች ከ184 ሄክታር በላይ መሬት አዘጋጅቷል፡፡

በከተማዋ ያለው አሁናዊ ሠላምና መረጋጋት፤ የህዝቡ የፍቅር አቀባበልና አብሮነት፤ የልማትና የብልጽግና ጉጉት ጊዶሌን እጅግ ተፈላጊ ያደርጋታል።


 

በመሆኑም የነገዋ ጊዶሌ የቀጠናው የመጻኢ-የብልጽግና ተምሳሌት ከመሆኗም በላይ ታሪክ፣ እሴት፣ ባህልና ኪነ-ጥበብ የተሰናሰሉባት የነገዋ የደቡብ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ማዕከል የመሆን ርዕይ ሰንቃለች::

ቀጣይ የልማት የብልጽግናና የተስፋ ማዕከል የሆነቺው ጊዶሌ በሎጅ እና ሆቴል፣ በነዳጅ ማደያ፣ በሱፐርማርኬት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በፋብሪካና እንዲሁም በተለያዩ መስኮች መዋዕለ-ንዋያችሁን ለማፍሰስ ለተዘጋጁ ኑ አልሙ፣ ኑ-እደጉ አብረንም እንደግ ትላለች፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም