ቀጥታ፡

የገጠር ኮሪደር ዕውን ለማድረግ 'የብልጽግ አርሶ አደሮች መንደር' በተሰኘ ንቅናቄ ወደ ስራ ተገብቷል - አቶ ዑስማን ሱሩር

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገጠር ኮሪደር ዕውን ለማድረግ 'የብልጽግ አርሶ አደሮች መንደር' በተሰኘ ንቅናቄ ወደ ስራ መገባቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኅላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የገጠር ኮሪደር ልማትን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የገጠር ኮሪደር የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ ውብና ጤናማ የገጠር ከባቢ በመፍጠር የተሟላ ብልጽግና ማረጋገጥን ያለመ ነው። 

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የገጠር ኮሪደር ዕውን ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኅላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር  ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ጽዱ አካባቢ መፍጠር፣ ንጹህ ልብስ መልበስ፣ ጥሩ ምግብ ማግኘት ከተማ ብቻ ሳይሆን ዋናው ሀብት የሚፈጠርበት ገጠር ጭምር ያስፈልጋል።

በበዚህም በክልሉ ከገጠር ኮሪደር ጋር የተሳሰረ 'የብልጽግ አርሶ አደሮች መንደር' ንቅናቄ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል። 

'የብልጽግ አርሶ አደሮች መንደር' ኢኒሸቲቭ ዓላማ አርሶ አደሩ ያካባቢውን ጸጋ በማልማት ኑሮውን እንዲያደላድል እና በምቹ፣ ጽዱና ውብ አካባቢ መከተል ማስቻል ነው።

በመሆኑም ክልሉ ይህን በተመረጡ መንደሮች የተጀመረውን ንቅናቄ አስፍቶ በመተግበር የገጠር ኮሪደርን ዕውን ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት።

የገጠር ኮሪደር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ከተመራና ምቹ አካባቢ በመገንባት የሰዎች ፍልሰትን ከገጠር ወደ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከከተማ ወደ ገጠርም የሚሆንበት ዕድልም ይፈጠራል ብለዋል።

በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማትን ዕውን ለማድረግ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ማሳያዎች እንዳሉ የጉራጌ ማህበረብ ባህላዊ ጎዳናን (ጆፎረ) እና የወጣት አብነት ዴላሞን መንደር ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ ግብርናን በማጠናከር አርሶ አደሩ ሀብት እንዲፈጥርና የዘመነ የኑሮ ዘይቤ እንዲከተል ማድረግ እንደሚቻል ነው የተናገሩት።

የገጠር ኮሪደር ለመተግበር በዙ ሀብትና መሰረተ ልማት አይጠይቅም ያሉት አቶ ዑስማን፤ ትልቁ ቁምነገር አስተሳሰብን መለወጥና አካባቢን ጸጋ መመልከት እንደሆነ ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአይቻልም አስተሳሰብ በመስበር ጅምሮችን በማስፋትና በማጽናት የገጠር ኮሪደርን ዕውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም