ቀጥታ፡

ባለሃብቶች በኮሬ ዞን ያሉ  አቅሞች እና እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲያለሙ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ባለሃብቶች በኮሬ ዞን ያሉ አቅሞች እና እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲያለሙ የኮሬ ዞን ጥሪ አቀረበ

የፊታችን ሕዳር 29 የሚከበረውን 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አስመልክቶ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ይህንኑ በተመለከተ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ የክልሉ ዞኖች የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን  እየጎበኙ ነው።

ወደ ኮሬ ዞን የመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኬሌ ከተማ ሲደርሱ የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስታረቀኝ አንደባ ፣ የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አካላት እና የዞኑ  ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።


 

የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስታረቀኝ አንደባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዞኑ በበርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ጸጋዎች እንዲሁም ቱባ ባህሎችን የያዘ ነው።

ዞኑ በርካታ የልማት አቅምና ጸጋ ቢኖረውም በመሰረተ ልማት እጥረት ጎልቶ ያልወጣ አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ዞኑ ለተለያዩ የግብርና ስራዎች ምቹ መሆኑን ገልጸው የሶስት አየር ጸባዮች ባለቤት መሆኑን ጠቁመዋል።

ቡና፣ ፍራፍሬ፣ጤፍ፣በቆሎ፣ቦለቄ እና እንሰት በስፋት የሚመረትበት መሆኑን ገልጸዋል

ባለሃብቶች ክልሉ ያለውን ጸጋ አውጥቶ እንዲጠቀም በኮሬ ዞን ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮሬ ህዝብ ከለውጡ ወዲህ ሲጠይቅ የነበረው የአደረጃጀት ጥያቄ ተመልሶለት አሁን ላይ በዞኑ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም