የ'ፋይዳ' ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች 

የ'ፋይዳ' ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች - በአቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ አንደበት።

በትግበራ ላይ የሚገኘው የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ስያሜ ነው - ፋይዳ።

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ፅህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ "ፋይዳ የሚለው ቃል በፅህፈት ቤቱ የተመረጠው ለዕለት ከዕለት አጠቃቅም ገላጭና ምቹ በመሆኑ ነው" ይላሉ።

የ'ፋይዳ' ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም የሀገሪቷ ቋንቋዎች ወጥ በሆነ ስም እንደሚጠራም እንዲሁ።

'ፋይዳ' በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ያነሱት አቶ ዮዳሔ፤ መታወቅ ለግለሰቡም፣ ለማህበረሰቡም እንዲሁም ለተቋማት አገልግሎት ወሳኝ ፋይዳ እንዳለው ይገልጻሉ።

በባዮሜትሪክ መረጃዎች ወጥ በሆነ ማንነት መታወቅ፤ መተማመን በመፍጠር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትም ጉልህ አንድምታ እንዳለው ያነሳሉ።

በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅም ሁነኛ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።

'ፋይዳ' ለሀገሬው ዜጋም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ያለምንም የማንነት ልዩነት የሚሰጥ በመሆኑ፣ አቃፊና አካታች የመታወቂያ መንገድ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ።

በወንጀል መከላከል ረገድ የሚኖረው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለአብነትም በፍትሕ ተቋማት ዘንድ የማጭበርበር ድርጊትን በመቀነስ ቀልጣፋናና ትክክለኛ የፍትህ አገልግሎት ለመዘርጋት ያስችላል።

ፅህፈት ቤቱ መሰረታዊ ከሆኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር በመፈራረም የማስተሳሰር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮቴሌኮም፣ ባንኮችና መንግስታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የተቋማት አገልግሎት ጋር መተሳሰር ደግሞ የፋይዳ መታወቂያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማሳያ መሆኑን ያነሳሉ።

'ፋይዳ' ዲጂታል መታወቂያ በመሆኑ የታተመ ካርድ ወይም ወረቀት መያዝ ግዴታ አለመሆኑን በማንሳት አንድ ሰው ያለምንም ክፍያ ተመዝግቦ ባለ12 አሃዝ ቁጥሮች መለያ ከተላከለት የፋይዳ ባለቤት ነው ይላሉ። 

ነገር ግን በወረቀት ወይም በካርድ መልክ መታወቂያውን መያዝ የሚፈልግ ሰው፣ ከበይነ መረብ አውርዶ በግሉም ይሁን አትመው በሚሰጡ አካላት በኩል የአገልግሎት ክፍያ ከፍሎ መያዝ እንደሚችል ገልጸዋል።

የተላኩለት ቁጥሮች የጠፋበት ሰው ደግሞ በ*9779# በመደወል ቁጥሮችን ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።

በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ 'ፋይዳ' መታወቂያ መመዝገብ ግዴታ ባይኖረውም ተቋማት ግን ለአገልግሎታቸው የዲጂታል መታወቂያን እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ይችላሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ የፋይዳን መታወቂያ ለአገልግሎት አሰጣጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን አስታውሰው፤ ይህን ተከትሎም ከተማ አቀፍ የፋይዳ ምዝገባ ዘመቻ መጀመሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም ዜጎች ከተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ላለመስተጓጎል ለዲጂታል መታወቂያ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም