በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ45 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ45 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገለጸ

ሆሳዕና፤ ሕዳር 8/2017(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት አራት ወራት ከ45 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገለጸ።
'ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ' በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ወጣቶች የመስሪያና የማምረቻ መሳሪያዎች ድጋፍ ትናንት በሆሳዕና ከተማ አድርጓል፡፡
ድጋፉ በሀድያና ስልጤ ዞኖች በግብርና፣ በገራዥ፣ በእደ ጥበብና በእንጀራ ጋገራ ለተሰማሩ 26 ኢንተርፕራይዞች ግምቱ ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የጎሚስታ ማሽን፣ ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽኖች፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ፣ ጀነሬተር፣ የኤሌክትሪክ ምድጃዎች፣ የምግብ ቤት ቁሳቁስ፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎች መሆኑ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ ታምራት ተስፋሁን፣ በበጀት ዓመቱ ከ350 ሺህ በላይ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመው በተለይም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተሰማሩ ወጣቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ለወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልፀው የተደረው ድጋፍም ትልቅ እገዛ መሆኑን አስረድተዋል።
'ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ' ግብረ ሰናይ ድርጅት አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በሀድያና ስልጤ ዞኖች ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ መካከል ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በ50 ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩ መድረጉንም አክለዋል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ስራ ለጀመሩና ውጤታማ ለሆኑ 26 ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
በሆሳዕና ከተማ ኪታ እደ ጥበብ ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት መስከረም ገብሬ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በግብረ ሰናይ ድርጅቱ አማካኝነት በተሰጣቸው የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና በባህል አልባሳት ስፌት ስራ መሰማራታቸውን ተናግራለች፡፡
የተደረገላቸው ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሽን በስራቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ ችንደሚያግዛቸው ገልጻለች።