ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ፋይዳው ከሩጫም በላይ ነው - አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ትርጉሙ ከሩጫም በላይ ነው ሲል የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ገለጸ።

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በ1993 ዓ.ም የተጀመረና በየዓመቱ የሚከናወን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነው።

በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን በማፍራት የራሱን ድርሻ ማበርከቱም ይታወቃል።

የዘንድሮውንም ''የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ህፃናት'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ 50 ሺህ ተሳታፊዎችን በማካተት እየተካሔደ ይገኛል።

ውድድሩ ለታዋቂ አትሌቶችና ለነገ ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶች የስኬታቸው መነሻ እንደሆነም አትሌት ሃይሌ ገልጿል።


 

ወድድሩ ከሩጫነቱ ባሻገር በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት አትሌቶች ዲፕሎማቶች ታዋቂ ግለሰቦች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ለቱሪዝምና ለገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁሟል።

የዘንድሮው ውድድር ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑንና የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት 50ኛ ዓመትን በማስመልክትም፤ 50ሺህ ተሳታፊዎችን በመያዙ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግሯል።

በየዓመቱ የሚካሔደውና ዘንድሮም ለ24ኛ ጊዜ እየተካሔደ ያለው ታላቁ ሩጫ በተፋጠነ የኮሪደር ልማት ገጽታዋን እየለወጠች ባለችው አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የብዙዎቹን ቀልብ በሚስቡ ትዕይንቶች ታጅቦ ዛሬም ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም