በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አትሌት ቢንያም መሐሪና አትሌት አሳየች አይቼው አሸናፊ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አትሌት ቢንያም መሐሪና አትሌት አሳየች አይቼው አሸናፊ ሆኑ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2017(ኢዜአ)፦በዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በወንዶች አትሌት ቢንያም መሐሪና በሴቶች አትሌት አሳየች አይቼው አሸናፊ ሆነዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደውና 50 ሺህ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተጠናቋል።
የዘንድሮው ውድድር "የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ህፃናት" በሚል መሪ ሀሳብ መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሣ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በላይ ደጀንና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
ውድድሩን የወቅቱ የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬኒያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲችና ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች በሥፍራው በመገኘት ተከታትለውታል።
በውድድሩ በወንዶች የአምናው የውድድሩ አሸናፊ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ቢንያም መሐሪ 1ኛ በመውጣት ሲያሸንፍ፣ አዲሱ ነጋሽ 2ኛ እንዲሁም ይስማው ድሉ 3ኛ በመውጣት አጠናቀዋል።
በሴቶች አትሌት አሳየች አይቼው በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ የኔዋ ንብረት ሁለተኛ እንዲሁም ቦሰና ሙላቴ ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።