ቀጥታ፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ለባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል − ከንቲባ ከድር ጁሃር 

ድሬደዋ ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለተሰማሩ ባለሃብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ በተገነባ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ የተሰሩ ተሽከርካሪዎች ዛሬ በይፋ ተመርቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስክ የሚሰማሩ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

ባለሃብቶቹ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ከማሳደግ ባሸገር ለነዋሪዎች የስራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተኪ ምርቶችን በማምረት እና ወደ ውጭ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ የሚቻልበት ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባለሃብቶች የጀመሩት ስራዎች  ስኬታማ እንዲሆኑ አስተዳደሩ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ አስተዳደሩ ፈጣን አገልግሎት በመስጠትና የመሬት አቅርቦት በማመቻቸት ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል። 

እንደ ከንቲባው ከድር ገለፃ፤ ፋብሪካው በስራ ዕድል ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ሽግግርም አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የኤ.ኤም ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ኦብሳ አህመድ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በግማሽ ቢሊዮን ብር ተገንብቶ አምና ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል ።

ፋብሪካው ለ150 ባለሙያዎችና ሰራተኞች ቋሚ እና ለመቶ ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ  በመታገዝ የተገጣጠሙት ተሽከርካሪዎች በይፋ የተመረቁ ሲሆን፤ ለገበያ እንደሚቀርቡም ተገልጿል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም