ኢንዱስትሪዎች ካይዘንን በመተግበር ቀጣይነት ያለው የምርት ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባቸዋል- አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎች ካይዘንን በመተግበር ቀጣይነት ያለው የምርት ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባቸዋል- አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢንዱስትሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ካይዘንን በመተግበር ቀጣይነት ያለው የምርት ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የካይዘን ልህቀት ማዕከል የዘጠነኛውን ሀገር አቀፍ ሽልማት ስነ-ስርዓትና እና ውይይት አካሂዷል።
በዕለቱም የካይዘንን ዋና ዋና ተግባራት ሥልጠና በመውሰድ የተገበሩ 21 ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
በዕውቅና መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ካይዘንን በመተግበር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እንዲሻሻል እያደረጉ ነው ብለዋል።
ካይዘንን መተግበር ቀጣይነት ያለው ምርታማነት፣ ጥራት፣ አምራች የሰው ኃይል ማፍራትና ለቴክኖሎጂ ልማት መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ካይዘንን በመተግበር ቀጣይነት ያለው የምርት ዕድገትን ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የካይዘን ፍልስፍና ስርፀትን ለማሳደግ ከመቼው ጊዜ በላይ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ካይዘን መተግበር ከጀመረ ወዲህ 1 ሺህ 500 ተቋማት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ከብክነት መዳን መቻላቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱና በእውቅና ስነ ስርዓቱ ላይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ካይዘን ሰው በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ ለውጥና መሻሻልን አስቦ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ፣ ፈጠራና አዲስ አስተሳሰብን የሚያበረታታ እንዲሁም ሰፊ የለውጥ፣ የጥራትና የምርታማንት ንቅናቄን በመፍጠር ስኬታማ የሚያደርግ የአመራር ፍልስፍና ነው።
ምርትና አገልግሎትን ተወዳዳሪና ውጤታማ በማድረግ የጋራ ተልዕኮን ከማሳካት አካያ ከፍተኛና መካከለኛ አመራርን እንዲሁም ሰራተኞችን የሚያስተሳስር እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።