የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ማነቆ የነበሩ ጉዳዮችን ፈቷል - ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ማነቆ የነበሩ ጉዳዮችን ፈቷል - ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ማነቆ የነበሩ ጉዳዮችን መፍታቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለአካታች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት ወሳኝ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ ለኢንቨስትመንት ዝግ የነበሩ መስኮች ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል።
ለአብነትም በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር የተደረገው ማሻሻያ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ለውጭ ተቋማት ክፍት እንዲሆን መወሰኑ ባንኮችን ጨምሮ የፋይናንስ ዘርፍ ተዋናዮችን የሚስብ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራና የቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለምጣኔ ሃብቷ ዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ያደረገችው ማሻሻያ የውጭ አገራት ኩባንያዎችን ጨምሮ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ስራቸውን ይበልጥ እንዲያስፋፉ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ይበልጥ ምቹ ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ኢንቨስተሮችን መሳብ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ ሰው ኃይልና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉም ሌላኛው ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ዕድገት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው የባንክና የቴሌኮም ዘርፍን ጨምሮ በነባር ዘርፎችም ትልቅ የኢንቨስትመንት ዕድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የተከናወኑ ምቹ ሁኔታዎችን ጨምሮ በማሻሻያው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ማነቆ የነበሩ ጉዳዮችን በመፈታታቸው የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ይበልጥ ሊነቃቃ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
በኢትዮጵያ እየተቋቋመ ያለው የካፒታል ገበያ በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢንቨስትመንት መስፋፋትም ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለዕውቀትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ አበርክቶ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡