ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ በይርጋለም ያስገነባችው ፋብሪካ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር ነው -  አቶ ደስታ ሌዳሞ

ይርጋለም ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በይርጋለም ከተማ ያስገነባችው ፋብሪካ  ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑን  የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በቤተክርስቲያኗ የሲዳማ ሀገረ ስብከት በይርጋለም ከተማ  በ300 ሚሊዮን ብር የተገነባ የጽሩይ ሳሙናና ዲተርጀንት ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት  ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያስገነባችው ፋብሪካ  ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው፤ ለበርካታ ሰዎች ስራ እድል የሚፈጥር ነው።  

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የፋብሪካው ወደ ስራ መግባት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፤  በመንግስትና በቤተክርሲቲያኗ መካከል ያለውን ትብብር የሚያጠናክር ነው።


 

መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለመደገፍ የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ረገድ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሳሙናና ዲተርጀንት ኢንዱስትሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሃገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ግብዓት ከሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ጋር በማስተሳሰር በተገቢው እንዲያመርት ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው፤ በሃገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ለሃገርና ህዝብ የሚጠቅሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

 ዛሬ የተመረቀው  ፋብሪካም በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገባና ከ400 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር  መሆኑን ገልጸዋል።

በሃገረ ስብከቱ የይርጋለም ደብረታቦር ኢየሱስ ወ/ደብረ መንክራት ቅድስት አርሴማ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ቀሲስ እንደሻው አብርሃ፤ በአብያተ ክርስቲያናቱ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች የልማት ዘርፎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ከተመረቀው የሳሙናና ዲተርጀንት ፋብሪካ በተጨማሪ በይርጋለም ከተማ የሆስፒታል ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው፤ የልማት ስራዎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ  የተለያየ ሃገረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም