ቀጥታ፡

ማዕከሉ አስተማማኝ ሰላምና ፍትህ ለማስፈን ለሚከናወኑ ስራዎች ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከል አስተማማኝ ሰላምና ፍትህ ለማስፈን ለሚከናወኑ ስራዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ማዕከሉ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ሲሆን፤ የሰነድ፣ የዘረመል (ዲኤንኤ) ዲጂታል ፎረንሲክ፤ ስውር አሻራና ሌሎች ከፎረንሲክ ጋር የተያያዙ የምርመራና ምርምር ስራዎች የሚከናወኑበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፤ ማዕከሉ ከአፍሪካ ትልቁ የፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

የማዕከሉ መገንባት ቀደም ሲል ተበታትነው ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ከማምጣቱም በላይ በአዲስ መልክ የተቋቋሙ ዘመኑን የዋጁ የምርመራ ላብራቶሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በዋናነትም የሰነድ፣ የጦር መሳሪያ፣ የቃጠሎ አደጋ፣ የፍንዳታ፣ የዘረመል ወይም ዲኤንኤ፣ የዲጂታል ፎረንሲክ፣ የኬሚስትሪና የስውር አሻራና መሰል ለወንጀል ምርመራ ስራ አስፈላጊ የሆኑ የምርመራ ላብራቶሪዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የምርመራ ስራ ብቻ ሳይሆን በፎረንሲክ ምርምር ብቁ የሆነ የሰው ሃይል የማፍራት ኃላፊነት እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

የክልል የፖሊስ አቅምን ለመገንባት ለሙያው ብቁ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመል ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ስፍራ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ድጋፍና ዕገዛ ለሚፈልጉ የአፍሪካ አገራትና በፎረንሲክ ሙያ የበቁ ዓለም ላይ ያሉ ምሁራን ስልጠናና ምርምር የሚያደርጉበት ሆኖ መመቻቸቱንም ጠቁመዋል፡፡

በማዕከሉ የጦር መሳሪያ እና ልዩ ልዩ ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር መለሰ በዛብህ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በውስን መሳሪያዎች ይሰሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ዘመኑን የዋጁ በርካታ ቴክኖሎጂዎች መጨመራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

እነዚህን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀምም የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኬሚስትሪ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ረዳት ኢንስፔክተር ሐብተማርያም እሱባለው በበኩላቸው የማዕከሉ መገንባት ምቹ የሥራ ከባቢን እንዲኖራቸው ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡


 

የምርመራ መሳሪያዎች መሟላትም የወንጀል መመርምር አቅማቸውን በእጅጉ እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ውስብስብ ወንጀልን የመመርመር ሀገራዊ አቅምን በእጅጉ ከፍ የሚያደርግ መሆኑ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም