አኩሪ ባህሎችንና ታሪኮችን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል - የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን - ኢዜአ አማርኛ
አኩሪ ባህሎችንና ታሪኮችን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል - የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን

ሐረር ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ አኩሪ ባህሎችንና ታሪኮችን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን ገለጹ።
"ሴና ኦሮሞ ሐረርጌ" "SEENAA OROMOO HARARGEE" በሚል ርዕስ የታተመ መጽሃፍ ዛሬ ተመርቆ ለንባብ በቃ።
በአፋን ኦሮሞ "ሴና ኦሮሞ ሐረርጌ" በሚል የተፃፈው መጽሃፉ ታሪክን፣ ባህልን፣ ስለተደረጉና ስለነበሩ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት ትግልና የጀግኖች ትኩረት ያደረገ ነው።
መጽሃፉ በ10 ምዕራፎች ተከፋፍሎ 534 ገጾችን ያካተተና ስለ አካባቢው ሙዚቃ እድገት ታሪክ፣ ስለ አንጋፋ አርቲስቶች እና ሌሎች በትውልድና ስለተዘነጉ ታሪኮችና ጀግኖች የሚገልፅ ነው።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባዔ ሰዓዳ አብዱረሃማን በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በመጽሀፉ አኩሪ ባህል፣ እሴት፣ የትግልና የጀግኖች ታሪክ፣ ኪነ ጥበብና ሌሎችም ተሰንደዋል።
"የኦሮሞ አኩሪ ባህሎችንና ታሪኮችን ለትውልድ የማስተላለፍ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይከናወናል" ያሉት አፈ-ጉባኤዋ፤ በዛሬው እለት የተመረቀው "ሴና ሐረርጌ ኦሮሞ" መፅሃፍ ለሌሎችም እንደ አርዓያና ትምህርት የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ እንደገለጹት፤ የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ለረጅም ዓመታት ታሪክን ሲያጠና ቆይቶ መፅሐፉ በዛሬው እለት ለምረቃ በቅቷል።
መጽሃፉ የወል ትርክትን የያዘና ለወጣቱም አኩሪ ታሪኩን እንዲያውቅ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ "ህዝቡም መጽሃፉን ማንበብ ይኖርበታል" ሲሉም አመልክተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአካባቢው ተወላጅ መሀመድ አህመድ ቆዼ (ዶ/ር) እንደገለጹ፤ መጽሃፉ የአገር ግንባታ እና አገራዊ መግባባትን የሚያዳብሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያነሳሳ ነው።
የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት በበኩላቸው፤ ተቋሙ በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባህልና በኪነ ጥበብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
ተቋሙ ከተቋቋመ ጀምሮም 70 የሚደርሱ ጥናታዊ ስራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ እስካሁንም 21 መፃሕፍት ታትመው ለህዝብ እንዲደርሱ መደረጉን ገልጸዋል።
ከመፅሓፉ ሽያጭ የሚገኘው 7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች እንዲውልም ኢንስቲትዩቱ ቃል መግባቱን አቶ ዝናቡ አረጋግጠዋል።
በዕለቱም ስለ አንድነትና አብሮነት የሚያቀነቅነው የአርቲስት መሃዲ ሼካ 14ኛ አልበም ለምረቃ በቅቷል።
በስነ ስርዓቱ ላይም፣ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፣ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሀመድ፣ በየደረጃው የሚገኙ የኦሮሚያ እና የሐረሪ ክልል አመራር አባላት፣ ምሁራን፣ አባ ገዳዎችና አደ ሲንቄዎች እንዲሁም ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።