በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ
ድሬደዋ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የድጋፍ ዘመቻ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እንደ ሀገር በተገኙ ውጤቶችና ልምዶች እንዲሁም በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ላይ ለሁለት ቀናት ያካሄደው ውይይት ዛሬ ተጠናቋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረጉ የተቀናጁ ድጋፎች መሠረታዊ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በንቅናቄው ከኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ ለአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የተደረጉ የተለያዩ ድጋፎች በዘርፉ አበረታች ለውጥ እንዲመጣ ማስቻላቸውን ገልፀዋል።
በተደረጉ ድጋፎች በተለያዩ ችግሮች የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።
በዚህም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን እንዲቀር እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር መቻሉንም አንስተዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው፤ በንቅናቄው በተደረጉ ድጋፎች 18 የተዘጉና በግንባታ ላይ የነበሩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መመለሳቸውን ገልፀዋል።
ከነዚህ በተጨማሪ ከአስተዳደሩ መሬት ወስደው ወደ ግንባታ ያልገቡና በግንባታ ላይ የነበሩ በርካታ ባለሃብቶች በተደረገላቸው ድጋፍ ግንባታቸውን አጠናቀው ወደ አገልግሎት እየተሸጋገሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የድጋፍና የክትትሉ ስራ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከአምስት እስከ ስምንት መካከለኛና ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይ በኢንዱስትሪና በዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መካከል ያለውን ትስስርን ይበልጥ በማጠናከር በምርምርና ጥናት የተደገፉ ተወዳዳሪና ጥራት ያላቸውን ተኪ ምርቶች በማምረት የውጭ ምንዛሬን በስፋት ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል ።
ዘንድሮም እነዚህን አበረታች ውጤቶችን በማሳደግ ድሬዳዋ የአገሪቱ የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግር ዕውን የሚሆንባት ቀዳሚ ከተማ እንድትሆን እንረባረባለን ብለዋል።