ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት አመታት በተለያዩ የልማት መስኮች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - አቶ ጌቱ ወዬሳ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል ባለፉት አምስት አመታት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና በሌሎች የልማት መስኮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።

የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት "የሀሳብ ልዕልና ለሁለተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የፓርቲው 5ተኛ የምስረታ ዓመት በልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

ዕለቱን አስመልክቶ አቶ ጌቱ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በሌሎችም የልማት መስኮች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የፓርቲው መመስረት የኢትዮጵያ የመለወጥ ፍላጎት እውን የሆነበትና የብልፅግና ጉዞ የተጀመረበት ነውም ብለዋል።

ፓርቲው ወንድማማችነትና አብሮነትን በማጠናከር እውነተኛ ሕብረ-ብሔራዊነትን በተግባር በማረጋገጥ ቋንቋ እና የጋራ ማንነትን ለኢትዮጵያ ብልፅግና ምሶሶ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ብልፅግና ፓርቲ ፈተናዎችን በመቋቋም አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት።

የፓርቲው መመስረትን ተከትሎ በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት ታላላቅ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በፖለቲካ ረገድ ከፓርቲው ምስረታ በኋላ በክልሉ ከሴራ ፖለቲካ ወደ መርህ ፖለቲካ፣ ከመገፋፋትና ከጥላቻ ወደ ሰላምና አብሮነት እንድንሸጋገር አድርጎናል ብለዋል።

በኢኮኖሚ ረገድም በግብርና እና በቱሪዝም ልማት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም የትምህርት ጥራት ከማጎልበትና የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ከማረጋገጥ አንጻር የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።

በክልሉ "የሀሳብ ልዕልና ለሁለተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል በከተማና በገጠር የፓርቲውን 5ተኛ የምስረታ ዓመት በፓናል ውይይቶች ፣ በደም ልገሳ፣ በሰብል መሰብሰብ ፣ በኪነጥበብ ፣ በግጥም ፣ ኢግዚቢሽን ፣ በስፖርት ውድድሮች፣ ጽዳት ዘመቻን ጨምሮ በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ አበረታች ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ኃላፊው መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም