በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህፃናት ፓርላማ ተመሰረተ

 አሶሳ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የህፃናት ፓርላማ ዛሬ ተመሰረተ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላትና  ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ ህፃናት በተሳተፉበት የምስረታው መረሃ ግብር ላይ የፓርላማው አፈ-ጉባዔ፣ ምክትል አፈ-ጉባዔና ፀሐፊን ጨምሮ ሌሎችም የኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል።

በምስረታ መረሃ ግብር ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ- ጉባዔ አቶ መለሰ ኪዊ ባደረጉት ንግግር፤  ህፃናት መብቶቻቸው እንዲከበር ፓርላማው መመስረቱ ለህፃናት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።


 

የህፃናት  ፓርላማው እንዲጠናከር የክልሉ ምክር ቤት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አለምነሽ ይባስ ፤ የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናት ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉና ህገመንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ ፓርላማው ሚናውን እንዲወጣ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።


 

በህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህፃናት ፓርላማ አፈ- ጉባዔ ሆኖ የተመረጠው  ፋሀሌን አብዱረህማን ፤ ፓርላማው ህፃናትን ባሳተፈ አግባብ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማዳበርና የህፃናትን ማህበራዊ ተሳትፎ ለማጎልበት እንደሚሰራ ገልጿል።


 

ከህፃናት መብትና ደህንነት አንፃር ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ እንሰራለን ብሏል።


 

ከህፃናት ፓርላማ ምስረታው ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን "ህፃናት የሚነግሩን አለ እናዳምጣቸው" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም