ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ ከመስኖ ልማት ከ172 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ የመስኖ ዕምቅ አቅም ባላቸው አስር ክልሎች ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ በሚለማ መሬት ከ172 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት በሁሉም መስክ ስኬት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ የልማት፣ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የመንግስት የትኩረት መስኮች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኅን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በበጀት ዓመቱ በሁለም መስክ ስኬት ለማስመዝገብ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ የካሄደው የ100 ቀናት የተቋማት ዕቅድ አፈፃጸም ግምገማ ውጤት ይህንኑ መረጋገጡን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅረቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ የሚያስችሉ የልማት ዕቅዶችን ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዓመት ይሆናል ሲባል በሁለንተናዊ መልኩ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ከተረጅነትና ጠባቂነት መላቀቅ የሚያስችል መሰረት የሚጣልበት መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም ምቹና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሥርዓትን መፍጠር የሚያስችሉ የሰላምና የመሰረተ ልማት ግንባታ ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትልሞችን ለማሳካት በትምህርትና ጤና ጥራትና ተደራሽነት ላይ ያተኮረ የሰብዓዊ ግንባታ የማፋጠን ስራ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስብራቶች ከመሰረታቸው መፍትሔ ለመስጠትም የሽግግር ፍትሕና ሀገራዊ የምክክር ሂደቶችን ዕውን ለማድረግ ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እንድታንሰራራ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል በግብርናው መስክ የተጀመሩ ተነሳሽነቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነውን መሬት በዘመናዊ አስተራረስ ዘዴ ማረስ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቁጥር አንድ ስንዴ አምራች ሀገር ማድረግ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተያዘው የመኸር ወቅትም ከብክነት በጸዳ መልኩ ምርት ለመሰብሰብ ህብረተሰቡ እንዲረባረብ አሳስበዋል።

በተያዘው የበጋ ወራት መንግስት የበጋ መስኖን ማስፋት የሚያስችል የመስኖ ቦይ ጠረጋና ጥገናን ጨምሮ የግብዓት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም የመስኖ ዕምቅ አቅም ባላቸው አስር ክልሎች ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከ172 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ስራዎችን የበጋ ወራት የትኩረት ማዕከል በማድረግ በዶሮና በእንስሳት ሃብት ልማት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አንስተዋል።

በሌላ መልኩም የለውጡ መንግስት ለብዝሀ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት የሚያስችሉ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በገበታ ለሸገርና ለሀገር የተገነቡ የወዳጅነት፣ አንድነት፣ መስቀል አደባባይ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ሃላላ ኬላና የቤኑና መንደር ፕሮጀክቶች እውን መሆን ለቱሪዝም ዕድገት ትልቅ ብስራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም መሰረተ ልማት፣ የብሪክስ አባልነት እንዲሁም አህጉራዊና ቀጣናዊ ሚና ማደግ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስና ጉባኤን ለማስተናገድ ዕድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በመዲናዋ የተደረጉ ከረሃብ ነፃ ዓለምና የካፍ ጉባኤ፣ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስና መሰል ታላላቅ ዓለም አቀፍና አሕጉራዊ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት በማስገንዘብ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን መፍጠር ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የኮሪደር መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችም ጨለማን ወደብርሀን በመቀየር ለሰው ተኮር ልማት መሰረት የጣሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሰላሟን እያጸናች ልማቷን በማፋጠን ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አሁንም የሰላም በር አለመዘጋቱን ተናግረዋል።

በኦሮሚያና አማራ ክልል ጠብመንጃ ላነሱ ኃይሎች መንግስት በሩን ክፍት በማድረግ በሰላማዊ ውይይት ለመቋጨት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው አስገንዝበዋል።

መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ያልተቀበሉ የሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖችም በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ላይ ጉዳት በማድረስና በማስተጓጎል ህዝብ ጠልነታቸውን በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይም መንግስት የሽብርተኛና ጽንፈኛ ኃይሎች ላይ በሚወስደው ህግ የማስከበር እርምጃ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም