የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚለውን መርህ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚለውን መርህ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚለውን መርህ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሠላማዊት ዳዊት ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ሥራ አስፈጻሚ ዘጠነኛ መደበኛ ስብሰባውን በፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት አካሂዷል።
የኮሚሽኑን የሥራ አስፈጻሚ አባላት 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማስመልከትም የብልፅግና ፓርቲ የኢንስፔክሽንና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሠላማዊት ዳዊት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የፓርቲውን ህገ-ደንብ እና መመሪያዎችን ማክበርና መጠበቅ በሁሉም የሥራ መስክ ጠንካራ የሥራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ይረዳል ብለዋል።
የፓርቲውን መርህና ግብ ከማሳካት አኳያ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ሥራ ለመፍጸም የሚያስችለውን መዋቅር እስከታችኛው እርከን ድረስ መዘርጋቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በ2017 በጀት ዓመት “ጠንካራ ኢንስፔክሽን፤ ለጠንካራ ፓርቲ” በሚል በጀመረው ንቅናቄ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስራውን በውጤታማነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በፓርቲ ውስጥ የሚፈጸሙ የምደባና ሹመት እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ህገ-ደንቡን መሠረት አድርገው ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረጉን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የፓርቲውን ጤናማነት ማስጠበቅ፣ መገምገም፣ ስልጠናዎችን መስጠት እንዲሁም ግንዛቤ የማስጨበጥ ዓላማ ይዞ ስራዎቹን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋዋል።
ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን የማድረግ ዋና ዓላማ እንዲሳካም ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛልም ብለዋል።
ኮሚሽኑ ጠንካራ ኢንስፔክሽን ለጠንካራ ፓርቲ የሚለውን መርህ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።