የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተፋጠነ ነው

ሶቆጣ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን የብሄረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ። 

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት የብሄረሰብ አስተዳደሩ ህዝብ የረዥም ጊዜ ጥያቄ ሆኖ የቆየ ነው። 

የክልሉ መንግስት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ባደረገው የበጀት ድጋፍ የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ካለፈው ዓመት  አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ግንባታ በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ግንባታውን በተሟላ መንገድ በማከናወን በቀጣዩ ዓመት ለአገልግሎት ለማብቃት መታቀዱን አመልክተዋል። 

የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት በተቀመጠለት ጊዜ በጥራትና ፍጥነት ግንባታው እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአዳሪ ትምህርት ቤቱ መገንባትም በብሄረሰብ አስተዳደሩና አካባቢ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስቸል ነው ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰይፈ ሞገስ ናቸው። 

ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል። 

የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ እንየው እውነቱ በበኩላቸው፤ አዳሪ ትምህርት ቤቱ የመማሪያ ፣ የአስተዳደር፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የቤተ መፅሐፍትና ቤተ ሙከራ መገልገያ ክፍሎች ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 32 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል። 

ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በቀጣይ ዓመት  ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰቆጣ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ በሰቆጣ ወረዳ በ16 ሄክታር መሬት ላይ 18 ህንፃዎችና ሁለት የስፖርት ሜዳዎችን ጭምር በማካተት እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል። 

በአማራ ክልል ደብረ ታቦርና ፍኖተ ሰላም ከተሞች ተመሳሳይ አዳሪ ትምህር ቤቶች  በግንባታ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም