ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም ለዓለም ሰላምና መረጋጋት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መመሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።

በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 27 ከፍተኛ መኮንኖችን በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ለምርምር እና ስልጠና አገልግሎት ያስገነባው ዘመናዊ ህንፃ ተመርቋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ እና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መመሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን እንዳሉት፣ በኢንስቲትዩቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ናቸው።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነት እና ግጭት መንሰራፋት ፈተና በመሆኑ በጋራ መቆምን ይጠይቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት 75 ዓመታት በተሰማራችበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አኩሪ ድል በማስመዝገብ ለቀጣናውም ሆነ ለዓለም ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም ሰላም የምታበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አዛዥ ኮሎኔል ጌቱ ታዬ፣ በሰላምና ግጭት አፈታት አስተዳደር ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ 27 ከፍተኛ መኮንኖች ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ የተሰጣቸውን የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስልጠና በብቃት የተወጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖሪ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ለአፍሪካ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ብቁ የሰው ሀይል ለማፍራት የልህቀት ማዕከል ሆና መቀጠል አለበት ብለዋል።

የጃፓን መንግስት የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትን ለማጠናከር እ ኤ አ ከ 2013 ጀምሮ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ሚናዋ መልካም ልምድን በማካፈል የጎላ አበርክቶ ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) ፤ የዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ኢንስቲትዩት ለአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የላቀና የረጅም ጊዜ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል ብለዋል።

አዲስ የተገነባው ህንፃ ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን በብቃት መወጣት የሚችል ሀይል ለማፍራት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም