ቀጥታ፡

የፌዴራልና የክልል ኢንቨስትመንት አስፈፃሚዎች የምክክር መድረክ በሠመራ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሠመራ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦የፌዴራልና የክልል ኢንቨስትመንት አስፈፃሚዎች የምክክር መድረክ በሠመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

24ተኛው የፌዴራልና የክልል የኢንቨስትመንት አስፈፃሚዎች የምክክር መድረክ በሠመራ ከተማ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል። 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሸነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ይህ ዓይነት የጋራ የምክክር መድረክ ቅንጅታዊ አሠራሮችን በማጠናከር ተግባራት የሚከናወኑበት ነው። 

በተያዘው በጀት ዓመት በጋራ ለማከናወን የተለዩ 8 ስትራቴጂክ ግቦች መኖራቸውን ገልፀው ያሉበት የአፈፃፀም ደረጃ የሚገመገም መሆኑን ተናግረዋል። 

በዚህም መስተካከል ያለባቸውን በጊዜ ለማስተካከል እንዲሁም የተሻለ ውጤት የታየባቸውን ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በመድረኩ ምክክር እንደሚካሄድባቸው ገልፀዋል። 

ከግምገማ ባሻገር የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ምክክሩ በሀገራዊ ዕድገት ድምር ውጤት የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል። 

በዕለቱ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ መሐመድ በበኩላቸው መድረኩ ያሉንን ፀጋዎች በመጠቀም ማልማት እንድንችልና የተሞክሮ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚረዳም ተናግረዋል። 

አቶ አሊ አክለውም መድረኩ ተባብሮ የመስራት ዕድልን እንደሚፈጥር እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የተሻለ ስራን ለመተግበር እንደሚያግዝም ገልፀዋል። 

የአፋር ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኤይሻ ያሲን እንዳሉት የአፋር ክልል የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎች እና እምቅ ሃብቶች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው እነዚህን ለማልማት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሳተፉ ባለሃብቶችን ለመሣብ እየተደረገ ያለው ጥረት መቀጠሉን አስታውሰው በክልሉ የተለያዩ ኢንቬስተሮች በማዕድን፣ በግብርናና በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይም የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የኢንቨትመንትና የኢንዱስትሪ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም