በጋምቤላ ክልል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ- ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ- ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የህብረተሰቡን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
በአኝዋሃ ዞን አቦቦና በጆር ወረዳ ከ74 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የተገነቡ ሶስት የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ርዕሰ መስተዳድሯን ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት በተገኙበት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ እንዳሉት፤ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ የተጠናከረ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በተለይም የህዝቡ ዋነኛ ችግር የሆነውን የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የህዝቡን ፍላጎት ያገናዘበ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎትን በገጠርና ከተማ ተደራሽ ለማድረግ ግብ ተጥሎ ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል።
ዛሬ ለምረቃ የበቁት የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአካባቢዎቹ ያለውን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር የሚያቃልል መሆኑን ገልጸዋል።
የየአካባቢው ማህበረሰብ ፕሮጀክቶቹ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዲራዘም ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡዶል በበኩላቸው፤ የክልሉን ህዝብ የንፁህ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም በገጠርና ከተማ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ እስካሁን በተከናወነው ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአኝዋሃ ዞን በአቦቦና በጆር ወረዳዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ዛሬ ለአገልግሎት የበቁት ሶስቱ ፕሮጀክቶች ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው አስታውቀዋል።
ከ16 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ በየአካባቢው የነበረው የመጠጥ ውሃ እጥረት እንደሚያቃለል አብራርተዋል።
ከነዋሪዎች መካከል አቶ አለሙ ኡሬቦ በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የንፁህ የመጠጥ ውሃ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
መንግስት ያለባቸውን የውሃ ችግር በመረዳት በቀበሌያቸው የንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በማመቻቸቱ ችግራቸውን ለማቃለል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
መንግስት በአካባቢያቸው ያለውን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የሚያስችል የውሃ ተቋም መገንባቱ እንግልትና ወጪ እንደሚያስቀርላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አቻላ ኡጁሉ ናቸው።
ሶስቱ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድና በዋን ዋሽ ፕሮግራም መሆኑም ተመላክቷል።