ቀጥታ፡

የከተማዋ ወጣቶች በኮሪደር ልማቱ ላይ በመሳተፍ ነጻ የእውቀትና የጉልበት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

ጎንደር ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ በኮሪደር ልማቱ ላይ የእውቀትና የጉልበት አስተዋጽኦ በማበርከት ታሪካዊ አሻራቸውን እያሳረፉ መሆናቸውን የከተማዋ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የጎንደር ከተማ ወጣቶች በከተማዋ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት በመደገፍ ዛሬ ማለዳ ነጻ የጉልበት አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ወጣት ደሳለኝ ፍሰሃ በሰጠው አስተያየት እንደገለፀው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድልን የፈጠረ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ ለወጣቱ የስራ ተነሳሽነትን፣ የፈጠራና የከተማዋንም የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃ መሆኑን ጠቅሶ፤ በዚህ ታሪካዊ የልማት ስራ በመሳተፉና አሻራውን በማሳረፉ ኩራት እንደተሰማው ተናግሯል፡፡  


 

ወጣት ማርታ ተስፋሁን በበኩሏ፤ ''የኮሪደር ልማቱ ምሽት ጭምር መከናወኑ ወጣቱ ለአዲስ የስራ ባህል እንዲነሳሳ ምቹ የልማት እድል ይዞ የመጣ ነው'' ብላለች፡፡

በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በወጣቱ ዘንድ ትልቅ መነሳሳትንና ቁጭትን የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጻ፤ በኮሪደር ልማቱ በጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሏ ኩራት እንደተሰማት ተናግራለች፡፡

''ወደ ከተማው የመጡ የልማት እድሎች ቀጣይነት ኖሯቸው ወጣቱ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለሰላም አጥብቀን እንሰራለን'' ያለው ደግሞ ወጣት ቴዎድሮስ ናሁሰናይ ነው፡፡

የከተማዋ ወጣቶች ልማትና ሰላም ናፋቂ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል በባለቤትነት ስሜት ለልማቱ መሳካት የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ እንደሆነም አመልክቷል። 

የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሩ መሃመድ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ በከተማው ወጣቶች ዘንድ ሰፊ ድጋፍና ተቀባይነት ያገኘ የልማት ተግባር ነው ብለዋል፡፡


 

የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ሰፊ የቱሪዝም ሀብት ለማልማትና ለመጠቀም መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ በመሆኑ የከተማዋ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ልማቱን በመደገፍ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የከተማዋ ወጣቶች በሀሳብ፣ በእውቀትና በጉልበት ጭምር በመሳተፍ ሰፊ ንቅናቄ መጀመራቸውን ጠቁመው፤ የኮሪደር ልማቱ እስኪጠናቀቅም በአደረጃጀት የሚመራ የስራ ስምሪት ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

በጎንደር ከተማ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የፒያሳ አካባቢ የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከፒያሳ እስከ አየር ማረፊያ የሚሸፍነው ሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማትም በአሁኑ ወቅት ወደ ትግበራ ተሸጋግሮ የመንገድ ዳር አጥሮችንና ኮንቴይነሮችን የማንሳት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም