ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ዛሬ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሞሮኮ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 8 አምስተኛ ጨዋታዋን ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ታደርጋለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኘው ስታድ ማርትያር ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

በጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።

ቡድኑ 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ 27 ልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ከትናንት በስቲያ ኪንሻሳ መግባቱ ይታወቃል።

አሰልጣኝ መሳይ ወደ ኪንሻሳ ይዘው ካመሩት የመጨረሻ ተጫዋቾች ዝርዝር ቢንያም አይተን፣ አብዩ ካሳዬ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን መቀነሳቸው ይታወቃል።

ዋልያዎቹ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን ጨዋታው በሚደረግበት ስታድ ማርትያር ስታዲየም ትናንት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 8 እስከ አሁን ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች በሶስቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ እንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በአንድ ነጥብ በምድቡ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በ54 ዓመቱ ሄሜድ ሱሌይማን የሚመራው የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድን በአራት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ማክሰኞ ሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም ያደርጋል።

በዚሁ ምድብ ጊኒ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ ኮትዲቭዋር በሚገኘው ኢቢምፔ ኦሊምፒክ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በምድብ 8 የምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጋቻቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ12 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ማረጋገጧ የሚታወስ ነው። ጊኒ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋዋን ለማለምለም የግድ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ አንጎላ፣ ሴኔጋል፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስከ አሁን በአፍሪካ ዋንጫው መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።

48 አገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም